Fana: At a Speed of Life!

ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር ይገባል-የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ ሲል የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላለፈ፡፡

መልዕክቱም የተገኘውን ሰላም በመጠበቅ ኢኮኖሚውን ማሳደግ እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር ይገባል ብሏል፡፡

በዓሉን ስናከብር የክርስትና ሐይማኖታዊ አስተምህሮን በመተግበር፣ ባህላዊ የመረዳዳት እሴታችንን በማጠናከር፣ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት፣ አቅመ ደካሞችን በማሰብ እና በመንከባከብ ሊሆን ይገባል ብሏል፡፡

በመንግሥትና በህወሓት መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ሕዝቡ የሰላም አየር ማግኘቱና ከፍተኛ የኢኮኖሚ መነቃቃት መፈጠሩን ምክር ቤቱ አመላክቷል፡፡

በመሆኑም የተገኘውን ሰላም በመጠበቅ ኢኮኖሚውን ማሳደግ እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር ይገባል ነው ያለው ምክር ቤቱ፡፡

ለዚህም ሁሉም ዜጋ ለሰላም ዘብ መቆም እንደሚገባው ተገልጿል፡፡

የሰላም ስምምነቱ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ተሸጋግሮ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን የገለጸው ምክር ቤቱ÷ የሰላም ጥረቱ በአስተማማኝ መልኩ ተግባራዊ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስቧል፡፡

የብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ሁሉ አቀፍ አካታች ውይይቶች በየደረጃው እንዲካሄዱ የሚያደርግ መሆኑንና ለኮሚሽኑ ተልዕኮ መሳካትም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የበኩሉን እንዲወጣ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የተጀመረው የፀረ ሙስና ትግል ውጤታማ እንዲሆን፤ ብልሹ አሰራርና የኢኮኖሚ አሻጥር እንዲከስም ምክር ቤቱ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን በትጋት እንደሚወጣ ተጠቁሟል፡፡

ምክር ቤቱ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ ሲል የመልካም ምኞት መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.