Fana: At a Speed of Life!

የገና በዓል በክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ተከበረ

 

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል (የገና በዓል) በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በሚገኙ የክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ተከበረ፡፡

በተለያዩ የኃይማኖት ስርዓት ታጅቦ የሚከበረው ይህ በዓል ፥ እንደየስፍራው ባህላዊ ስራዓትን በተከተለ መንገድ በምዕመኑ ተከብሮ ውሏል፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ታስቦ በሚውልበት ቀንም የእምነቱ ተከታዮች ኃይማኖታቸው በሚያዘውና በሚፈቅደው ሁሉ በመተሳሰብና በምስጋና አክብረውታል፡፡

የኃይማኖት አባቶቹ የ2015 ዓ.ም የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በሚያስተላለፉበት ወቅት እንዳሉትም ፥ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የፍቅር እና የትህትና መሠረት በመሆኑ ክርስቲያን ምዕመኑ እርስበርስ በመፋቀር እና በመዋደድ በተግባር ሊተረጉመው ይገባል፡፡

እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ወደዚች ምድር መምጣቱ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር ማሳያ በመሆኑ እኛም እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያሳየውን ፍቅር ማሳየት ይገባናልም ነው ያሉት።

እርስበርስ መዋደድ በሰላምና በፍቅር መኖር አምላካዊ ትእዛዝ ነውና በመንፈሳዊና ዓለማዊ የስራ ኃላፊነት የምንገኝ ሰዎች የእግዚአብሔር ትእዛዙን ማክበር ግዴታችን ነው ሲሉም ነው የገለጹት።

በኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ በእግዚአብሔር እና በሰው ልጅ መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ የፈረሰበት መሆኑን አውስተው ፥ እናም በዓሉ የትህትናና የፍቅር በዓል እንደመሆኑ ክርስቲያን ምዕመኑ በተለያየ ምክንያት የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብና ካለው በማካፈል በዓሉን አብሮ ማሳለፍ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

በዕለት ዕለት እንቅስቃሴውም ለወገኑ በጎ ምግባራትን በማከናወን ኢየሱስ ክርሰቶስ ያሳየውን ተምሳሌትነት ሊተገብር ይገባል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.