Fana: At a Speed of Life!

ካለን ማካፈል ከራስ በፊት ለህዝብና ለሃገር የሚለውን ወርቃማ እሴታችን የምናሳይበት ነዉ – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ካለን ማካፈል ከራስ በፊት ለህዝብና ለሃገር የሚለውን ወርቃማ እሴታችን የምናሳይበት ነዉ ሲሉ የኢፌዴሪ መከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብራሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡

የገናን በዓል በማስመልከት በብላቴ ኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል አካባቢ ላሉ 120 አቅመ ደካማ ነዋሪዎች የዓይነት እና የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል።

የኢፌድሪ መከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚህ ወቅት ፥ ያለንን ማካፈል የኖርንበት የኢትዮጲያዊነት ባህላችንና እንደ ተቋም ከራስ በፊት ለህዝብና ለሃገር የሚለውን ወርቃማ እሴታችን የምናሳይበት ነዉ ብለዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሠራዊታችን አክለው እንዳሉትም ፥ ለሀገር ሰላም ሲል ውድ ህይወቱን የሚገብር ፤ ህዝቦቿ ሲቸግሩ ካለው የሚያካፍል የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጅ ነው።

ሠራዊታችን የሰላማችን ዘብ የቸገረን ጊዜ ረዳታችን ነው ፤ የገናን በዓል በማስመልከት ለተደረገልን ድጋፍ እናመሰግናለን ሲሉ ድጋፍ የተደረገላቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ድጋፉን የ40ኛ ዙር 1ኛ ብርጌድ ተመራቂ የኮማንዶ አባላት ያሰባሰቡ ሲሆን ፥ ከወላይታ ዞን እና ሲዳማ ክልል ውስጥ ካሉ 5 ቀበሌዎች ለተውጣጡ ነዋሪዎች መበርከቱን ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ÷ ለሀገር ሉዓላዊነትና ደህንነት ሲባል ኮማንዶ አየር ወለድና አየር ኃይልን ከምንጊዜውም በላይ ለማደራጀት ተዘጋጅተናል ሲሉ ገልፀዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ተመራቂዎች የሀገር አለኝታነታቸውን በተግባር ማረጋገጥ እንዳለባቸው አሳስበው ሀገራችን ሁሌም ሰላም ነው ምትፈልገው፤ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ነገር ቢያጋጥም ግን ያንን የሚመክት ኃይል በማሰልጠን በማስታጠቅና በማዘጋጀት ረገድ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

የኮማንዶና አየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል የሪፐብሊካን ጥበቃ ኃይልን ከማሰልጠንና ከማጠናከር ባለፈ በህገ-መንግስቱ በተሰጠው ተልዕኮ መሠረት የፌዴራልና የክልሎችን የፀጥታ ኃይል አቅም በመገንባት ላይ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ ናቸው።

ኢትዮጵያን በሚመጥን ደረጃ የስልጠና አሰጣጥ ሒደቱን እያዘመነ ጠንካራ ተዋጊ ኮማንዶ አየር ወለድና ልዩ ኃይል ፀረ-ሽብር የማሰልጠን ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል ሌተናል ጀነራል ሹማ ።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.