ዓለምአቀፋዊ ዜና

ቻይና በኮቪድ-19 ሳቢያ ያሳለፈችውን የውጭ ሀገር የጉዞ ገደብ አነሳች

By Alemayehu Geremew

January 08, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ያሳለፈችውን የውጭ ሀገራት የጉዞ ገደብ አነሳች፡፡

ከአሁን በኋላ ወደ ቻይና የሚገቡ የውጭ ሀገር ተጓዦች ቀደም ሲል በተቀመጠው የኮቪድ -19 አስገዳጅ መመሪያ መሠረት በለይቶ ማቆያ ለአምሥት ቀናት እንደማይቀመጡ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

ቢጂንግ ገደቡን ካነሳች ወዲህ የመጀመሪያዎቹን 387 መንገደኞች ከሲንጋፖር እና ከካናዳዋ ቶሮንቶ ከተማ መቀበሏ ተመላክቷል፡፡

መንገደኞቹም ቀደም ሲል በሀገሪቷ በተጣለው የኮቪድ -19 ገደብ መሠረት ሳይንገላቱ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር መቀላቀላቸው ነው የተገለጸው፡፡

ቀደም ሲል ቻይና እየተባባሰ በሄደው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሥርጭት ምክንያት ድንበሮቿን ላለፉት ሦስት ዓመታት ዘግታ መቆየቷ ይታወሳል፡፡