Fana: At a Speed of Life!

የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ባለዕድለኞችን ውል ማዋዋል ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ባለዕድለኞች ውል ማዋዋል ስራ በዛሬው ዕለት መጀመሩን የአዲስ አበባ ቤቶች እና ልማት አስታዳደር ቢሮ አስታውቋል፡፡
 
በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በ20/80/ ለ14 ኛ ጊዜ እና በ40/60 ለ3ኛ ጊዜ ባለፈው ሕዳር ወር 2015 ዓ.ም. የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እጣ ማውጣቱ ይታወቃል ፡፡
 
በዚህም የ20/80 መርሐ ግብር 18 ሺህ 930 ቤቶች እና የ40/60 ደግሞ 6 ሺህ 843 ቤቶች ባለ እድለኞች መለየታቸው የሚታወስ ነው፡፡
 
እነዚህን ባለ ዕድለኞች ከዛሬ ከጥር 1 ቀን 2015 ዓ/ም ጀምሮ ውል ማዋዋል ስራ መጀመሩን የአዲስ አበባ ቤቶች እና ልማት አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል፡፡
 
የውል ማዋዋል ስራው ከዛሬ ጀምሮ ለ60 የስራ ቀናት ወይም ለሁለት ወራት ጊዜ ብቻ እንደሚካሄድ ነው ቢሮው ያስታወቀው፡፡
 
ስለሆነም ባለ ዕድለኞች መገናኛ በሚገኘው ቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ግቢ ውስጥ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ በመምጣት ውል መዋዋል እንዳለባቸው ተመላክቷል፡፡
 
በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ቀርቦ ያልተዋዋለ እድለኛም በመመሪያ ቁጥር 3.3/2011 መሰረት ቤቱን እንዳልፈለገው ተቆጥሮ ተመላሽ እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡
 
ባለ ዕድለኞች ማሟላት የሚገባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በአንድ ማዕከል የአገልግሎቱ መስጫ ማግኘት እንደሚችሉም ቢሮው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አስታውቋል፡፡
 
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.