Fana: At a Speed of Life!

በተለያዩ አካባቢዎች በባህላዊ መንገድ የሚመረተው የወርቅ ምርት ለህገወጥ ግብይት የተጋለጠ ነው-ኢ/ር ታከለ ዑማ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በባህላዊ መንገድ የሚመረተው የወርቅ ምርት ለህገወጥ ግብይት የተጋለጠ ነው ሲሉ የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ዑማ ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘውንና ግዙፉን ኩርሙክ የወርቅ ኩባንያ ግንባታ መጎብኘታቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡

ህገወጥ የወርቅ ግብይት መቆጣጠር በሚቻልበት መንገድ ዙሪያም ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን እና ከፌደራል መንግስት ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ነው የገለጹት፡፡

ችግሩ የብዙዎችን ቅንጅት የሚፈልግ በመሆኑም በተቀናጀ መልኩ ለመስራት መግባባት ላይ ደርሰናል ነው ያሉት ፡፡

በቅርቡ እንደሚፀድቅ የሚጠበቀው አዲሱ የማዕድን ልማት አዋጅም ይህንና ሌሎች ችግሮችን በተደራጀ መልኩ ለመከላከል የሚያግዘን ይሆናል ብለዋል፡፡

ኢንጂነር ታከለ በማዕድን ክፍለ ኢኮኖሚ የተረጋጋ ኢኮኖሚ ግንባታን በትብብር ማሳካት እንደምንችል የዛሬው ጉብኝታችን ትልቅ ማሳያ እና ተስፋ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በጉብኝት መርሐ ግብሩ ከኢንጂነር ታከለ ኡማ እና ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በተጨማሪ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

ኩርሙክ የወርቅ ፋብሪካ በ14 ቢሊየን ብር ወጪ እየተገነባ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.