በደቡብ ክልል በ6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች ከ2 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ድምፅ ሰጪዎች ተመዝግበዋል – ቦርዱ
አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል በ6 ዞኖች እና በ5 ልዩ ወረዳዎች ለሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ 2 ሚሊየን 934 ሺህ 143 ሰዎች ድምፅ ለመስጠት መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡
ቦርዱ በደቡብ ክልል ውስጥ በሚገኙ የኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦ እና ጎፋ ዞኖች እንዲሁም በቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ እንዲሁም ደራሼ ልዩ ወረዳዎች የሚካሄደውን ሕዝበ ውሣኔ በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርትኳን ሚዴቅሳ፥ 3 ሺህ 769 መደበኛና 7 የተፈናቃይ ጣቢያዎች መለየታቸውንም አመላክተዋል፡፡
የተፈናቃይ መራጮች ምዝገባ የተካሄደው በኮንሶ ፣ አሌና ደራሼ አከባቢ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በሂደቱ ካጋጠሙ ችግሮች መካከል በ24 ምርጫ ጣቢያዎች የኅግ ጥሰቶች በመፈጸማቸው የቀድሞው ምዝገባ ውድቅ መደረጉ ነው የተመላከተው፡፡
የምርጫ አስፈፃሚዎች ተቀይረው በድጋሚ ምዝገባው በ24ቱ ጣቢያዎች እንዲካሄድም እስከ ጥር 3 ቀን 2015ዓ.ም ድረስ ጊዜ ተቆርጧል፡፡
2 ሚሊየን 934 ሺህ 143 መራጮች የተመዘገቡት ከ24ቱ ጣቢያዎች ውጭ መሆኑም የተገለፀ ሲሆን፥ በህዝበ ውሳኔው 5 ሺህ 274 የሀገር ውስጥ ታዛቢዎች ይሰማራሉ ነው የተባለው።
በአሸናፊ ሽብሩና ሳሙኤል ወርቃየሁ