27 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ካሊፎርኒያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ሀኪሞች 27 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደርገዋል፡፡
ድጋፉን በሰሜን ካሊፎንያን የሚገኙ የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎችን እና ኢትዮጵያዊያን ኮሚዩኒቲ አባላትን በመወከል የመጡት ዶ/ር ቅድስት ኪዳኔ ለጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ አስረክበዋል።
ዶክተር ቅድስት ኪዳኔ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያዊያን ኮሚዩኒቲ አባላት ቀደም ብለው ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ድጋፉን ማሰባሰብ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
ድጋፉ በዋግ ህምራ እና ሰሜን ወሎ አካባቢ ለሚገኙ አራት ጤና ጣቢያዎች የሚውል መሆኑን ገልፀው÷ በአጠቃላይ 27 ሚሊየን ብር የሚያወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የጤና ሚኒስተሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው÷ ድጋፉ ጤና ጣቢያዎችን ሙሉ ለሙሉ አደራጅቶ ወደስራ ለማስገባት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሚያደርጉት ድጋፍ መንግስት በጦርነቱ የተጎዱ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ለሚያከናውናቸው ተግባራት አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ሚኒስትሯ÷ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት መልሶ ለማቋቋም ለሚከናወኑ ተግባራት እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ ማቅረባቸው ኢዜአ ዘግቧል፡፡