Fana: At a Speed of Life!

የጥምቀት በዓል በጎንደር ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር አስተማማኝ ዝግጅት ተደርጓል-ፖሊስ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጥምቀት በዓል በጎንደር ከተማ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የአማራ ክልለ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ የሚዲያ ዋና ክፍል ኃላፊ ም/ኮማንደር መሳፍንት እሸቴ እንደገለጹት÷ የጥምቀት በዓልን በጎንደር ለማክበር በርካታ የውጭ እና የሀገር ውስጥ እንግዶች ወደ ከተማዋ እየገቡ ነው፡፡

እንግዶቹ በዓሉን ደኅንነታቸው ተጠብቆ በሰላም እንዲያከብሩም ፖሊስ ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር ዕቅድ አውጥቶ በቅንጅት እየሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በዚህ መሰረትም ከፌደራል ፖሊስ፣ ከአማራ ፖሊስ፣ ከከተማዋ አድማ ብተና እና ሚሊሻ የተውጣጣ ጥምር ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በጎንደር ከተማና አካባቢው በሚገኙ የሕብተሰብ ክፍሎች አደረጃጀት በመፍጠር እስከ ሰፈር ድረስ መዋቅር መሠራቱን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ጠንካራ አደረጃጀት እና የትብብር መንፈስ በነዋሪዎች ዘንድ መፍጠር መቻሉን ነው ምክትል ኮማንደሩ የተናገሩት፡፡

የጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አየልኝ ታክሎ በበኩላቸው÷ የከተማዋ ፖሊስ ለበዓሉ በስኬት መጠናቀቅ ድጋፍ ያደርጋሉ ካላቸው የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራት ጋር መወያየቱን አንስተዋል፡፡

በየትኛውም ሁኔታ የእንግዶችን ጸጥታ የሚያደፈርሱ ሁነቶችን ለመቆጣጠር አደረጃጀቶችና ሕበረተሰቡ የፖሊስን ተግባር ተክተው በሚሠሩበት አግባብ ላይ መደረሱንም ጠቅሰዋል፡፡

ሆቴሎችን ጨምሮ ሁሉም አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም እንግዶችን ለመቀበል አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ጎንደር ለበዓሉ ምንም አይነት የጸጥታ ስጋት እንደሌላት የገለጹት ረዳት ኮሚሽነሩ፥ የጥምቀትን በዓል ለማክበር የሚመጡ እንግዶችም በነጻነትና በሰላም በዓሉን አክበረው መመለስ እንደሚችሉ አረጋግጠዋል፡፡

የከተማዋን ሰላም እና ደኅንነት መጠበቅ የሁሉም ህብረተሰብ ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመው፥ ሕብረተሰቡ በእያንዳንዱ ሁኔታ ላይ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በቅንጅት እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.