የሀገር ውስጥ ዜና

የስኳር ምርት እጥረትን ለመቅረፍ እየተሠራ ነው

By ዮሐንስ ደርበው

January 11, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በድጎማ የሚቀርበውን የስኳር ምርት እጥረት ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የሕዝብ ግንኙነትና ተሳትፎ ዋና ክፍል ኃላፊ ረታ ደመቀ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ በድጎማ የሚቀርበውን የስኳር ምርት እጥረት ለመቅረፍ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡

አራት የስኳር ፋብሪካዎች ከሁለት ሣምንት በፊት በከፊል ሸንኮራ አገዳ የመፍጨት አቅማቸው እየሠሩ ማምረት መጀመራቸውን እና በአጭር ጊዜ በሙሉ አቅም ወደ ማምረት እንደሚሸጋገሩ ገልጸዋል፡፡

ከጥር ወር አጋማሽ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ተጨማሪ አራት ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንደሚገቡ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

እንዲሁም ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የስኳር ምርት ለማስገባት ሌሎች ሒደቶች መጠናቀቃቸውን እና የመተማመኛ ክፍያው በአቅራቢው ኩባንያ ለባንክ እንደተፈጸመ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገዛው 2 ሚሊየን ኩንታል ስኳር መጫን እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡

በአራት ዙር ወደ አገር ገብቶ እንደሚጠናቀቅም ነው አቶ ረታ የተናገሩት፡፡

የስኳር ምርት ፍላጎት በሀገር ውስጥ በማምረት እና ከውጭ በማስገባት እየተሸፈነ መሆኑን ጠቁመው፥ በ2020 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ የስኳር ምርት ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ለመሸፈን ታቅዷል ብለዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!