የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል እና የኮማንዶና አየር ወለድ ኃይል ተልዕኳቸውን በውጤት ፈጽመዋል
አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኅልውና ማስከበር ዘመቻዎች የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል እና የኮማንዶና አየር ወለድ ኃይል የተሰጣቸውን ተልዕኮ ከሌሎች የሠራዊት ክፍሎች ጋር በመናበብ በውጤት መፈፀማቸውን ሜጄር ጄኔራል አብድሮ ከድር ተናገሩ፡፡
የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል ለኮማንዶና አየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል አሠልጣኞች የምስጋና ሥነ ስርዓት አካሂዷል፡፡
የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል ምክትል አዛዥ ለሰው ሃብት ልማት ጠቅላላ አገልግሎት ሜጄር ጄኔራል አብድሮ ከድር በሥነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የብላቴ ኮማንዶና አየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል በየጊዜው የተቋሙን የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማሟላትና የዘመናዊ ሠራዊት ግንባታ ሂደት ግቡን እንዲመታ በትጋት እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
“ባሳለፍናቸው የኅልውና ማስከበር ዘመቻዎች የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል እና የኮማንዶና አየር ወለድ ኃይል የተሠጣቸውን ተልዕኮ ከሌሎች የሠራዊት ክፍሎች ጋር በመናበብ በውጤት ፈጽመዋል ” ማለታቸውን የመከላከያ ሠራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡
ጄኔራል መኮንኑ አክለውም÷ አሰልጣኞች ለክፍላችን ሁለንተናዊ ዝግጅት እና ግንባታ ላደረጋችሁት ላቅ ያለ አስተዋፆና ድጋፍ በሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል ስም እናመሰግናለን ብለዋል፡፡
የብላቴ ኮማንዶና አየር ወለድ ኃይል ማሰልጠኛ ማዕከል አዛዥ ኮሎኔል ቦጃ አጋ እንደገለጹት÷ ማሰልጠኛ ማዕከሉ የተቋሙን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በየጊዜው ብቁና ታታሪ የኮማንዶና አየር ወለድ አባላትን በማሰልጠን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማሰጠበቅና ጠንካራ የኮማንዶ ኃይል ለመገንባት ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ ነው፡፡