Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የአብሮነት ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2015 (ኤፍቢ ሲ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ከጎንደር ከተማ አስተዳደር እና ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የአብሮነት ውይይት ተካሄደ፡፡

የአብሮነት ውይይቱ ፥ “የሃይማኖቶች አብሮነት ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ትብብር” በሚል መሪ ሐሳብ ነው በጎንደር ከተማ የተካሔደው፡፡

በመርሐ- ግብሩ የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ÷ ባለፉት ዓመታት በብዙ ምክንያቶች እንዳንስማማና እንድንጋጭ ሆነናል ሲሉ ተናግረዋል።

ወላጅ ከልጅ ጋር ሃይማኖት ከሃይማኖት ጋር እንዳይስማሙ ተደርጎ ቆይተናል ያሉት ከንቲባው ፥ ከዚህ ሁሉ ያተረፍነው የለም ፤ ከክብራችን ዝቅ አልን እንጂ ሲሉም ነው የገለፁት።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን በበኩላቸው ÷ ለተሻለ የዜጎች ህይወት በመሪነት ደረጃ ላይ ያሉ ልሂቃን ሊበረቱ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሃሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶችን የምንፈታበት ስርዓት ካላበጀን ጥቃቅን ልዩነቶች እየከረሩ ሄደው ግጭት መውለዳቸው ስለማይቀር ሁሉም አካላት በኃላፊነት ጠንክረው ለሰላም መስራት አለባቸው ብለዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲም ከተቋቋመበት ዓላማ አኳያ በማህበረሰብ አገልግሎት ለሰላም፣ ለልማትና ለህብረተሰብ ግንባታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ስራውን ይቀጥላልም ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሀፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ÷ እኛ ኢትዮጵያውያን ጠንካራ ባለታሪክና ለምንም ነገር የማንረታ ስንሆን የጋራ አብሮነታችን እሴትም የሚያብብ ነው ብለዋል፡፡

ይህ እሴታችን ጠንክሮ እንዲቀጥልም በጋራ መስራት ይኖርብናል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔም ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ተግባራትን ሲሰራ የቆየናአሁንም እየሰራ ይገኛል በማለትም የአብሮነትና መተባበር ስርዓቶች ሁሉ ተጠብቀው እንዲቀጥሉም እየሰራ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡

የሃይማኖት አባቶች፣ የእምነት ተቋማት መሪዎች፣ የፌዴራልና የከተማዋ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በውይይቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡

በውይይቱ÷ ሰላምና አብሮነትን በተመለከተ የጎንደር ከተማ የሰላም ኮሚቴ እንቅስቃሴ የሚዳሰስ ሲሆን÷ የቀጣይ የጋራ ተግባራትና የአብሮነት ጉዞዎች ምከረ ሐሳብ እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡

በሙሉጌታ ደሴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.