Fana: At a Speed of Life!

የሸኔን ፍላጎት ለማምከን የሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች ከሃይማኖት አባቶችና ሀገር ሽማግሌዎች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽብር ቡድኑን ሸኔ ፍላጎት ለማምከን የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ አንገር ጉቴ ከተማ ከሃይማኖት አባቶችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
 
በአሸባሪው የሸኔ ቡድን ሴራ በንፁሃን ላይ እየደረሠ ያለውን ግድያና መፈናቀል በአጭር ጊዜ ለማስቆምና ሠላምን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጄኔራል መኮንኖች በምስራቅ ወለጋ ዞን በጊዳ አያና ወረዳ አንገር ጉቴ ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ የሃይማኖት አባቶች ከሀገር ሽማግሌዎችና ከወጣቶች ጋር መክረዋል።
 
በምክክር መድረኩ ጄኔራል መኮንኖች ህብረተሰቡ በሀሠተኞች ፕሮፖጋንዳ ሳይሸበር የሀገርን እና የህዝብን ሠላም ለማረጋገጥ ከተሠለፈው ጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን ጋር በመሆን እንደ ከዚህ ቀደሙ አብሮነቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ ገልፀዋል።
 
በተሳሳተ እሳቤ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚፈልጉና የሀገራችንን ሠላም መሆን የማይመኙ የጥፋት ሃይሎች በህዝባችን ላይ እንዲፈነጩ እድል አንሰጣቸውም፤ አንፈቅድላቸውም ማለታቸውንም የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል።
 
የመድረኩ ተሳታፊዎች ለሀገራችን ሠላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ የአካባቢያችን የፀጥታ ሃይል ማጠናከርና ለሠራዊታችን ደጀን በመሆን ኢትዮጵያን በድል ለቀጣይ ትውልድ ማሻገር የመጀመሪያው ተግባራችን ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
 
የሃይማኖት አባቶች አሸባሪው የሸኔ ቡድን ለረዥም ጊዜያት በፍቅር አብረው የኖሩትን የኦሮሞና የአማራን ህዝብ ለማጋጨት የሚያደርጉትን ህገ ወጥ ተግባር እናወግዛለን ከሠራዊታችን ጎን እንቆማለን”ሲሉ ገልጸዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.