የኑሮ ውድነትና የስራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት ምርታማነት ላይ አተኩሮ ይሰራል- ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የኑሮ ውድነትና የስራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት ምርታማነት ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ፡፡
“ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል በደብረ ብርሃን ከተማ ከአምራች ኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፉ ባለሃብቶች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ÷ በርካታ ኢንዱስትሪዎች እየተከፈቱ መሆኑን ገልፀው ይህንን ለመመገብ የግብርናው ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል፡፡
የኢንዱስትሪዎች ፍሰት እየጨመረ ቢሆንም አብዛኛው ወደስራ አልገቡም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ የዛሬው ውይይትም ይህን ችግር ለመፍታት ያለመ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ÷ የግል ባለሃብቱ ያለበትን የፋይናንስና የመሬት አቅርቦት ችግር ለመፍታት የክልሉ መንግስት ይሰራል ያሉ ሲሆን÷ ባለሃብቱም ከአመራሩ ጋር ተናቦ ለሀገሩ ልማት መስራት ይጠበቅበታልም ብለዋል፡፡
በውይይቱ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች የክልልና የፌደራል ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
በዘላለም ገበየሁ