የሀገር ውስጥ ዜና

ሀገር አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር በሐዋሳ ከተማ ተከፈተ

By Feven Bishaw

January 12, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመጀመሪያ ዙር ሀገር አቀፍ የጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽን እና ባዛር በሐዋሳ ከተማ ተከፍቷል።

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጪ የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን÷ ኤግዚቢሽንና ባዛሩን በሀዋሳ ከተማ ማዘጋጀት ያስፈለገው ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እና ለማስፋት፣ ሀገራዊ ኤግዚቢሽንና ባዘሮችን ከማዘጋጀት አኳያ የክልሎችን ልምድና አቅም ለማሳደግ እንዲሁም ሁለንተናዊ የሆነ ቀጠናዊ ትስስርን ለማጎልበት ነው ብለዋል።

የገበያ ትስስር መፍጠር አንዱና ዋነኛው የመንግስት የድጋፍ ማዕቀፍ መሆኑን ያነሱት የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ፥ ባዛሩ በዚህ መዘጋጀቱ ለክልሉ ትልቅ የኢኮኖሚ መነቃቃት ከመፍጠርም ባለፈ ለአነስተኛና ጥቃቅን ትልቅ ልምድ የሚሆን ነው ብለዋል።

ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 224 ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ፣ 22 አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉበት ይህ ኤግዚቢሽን ለሐዋሳ ከተማ ገበያን ከማረጋጋት ባለፈም ትልቅ የቱሪዝም ትርፍም እንደሚኖረው ገልፀዋል።

ኤግዚቢሽንና ባዛሩን ከ35 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚጎበኙትና በርካታ የገበያ ትስስር እንደሚፈጥር ታምኖበታል፡፡

በጥላሁን ይልማ