Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን የሰብዓዊና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች ድጋፍ እንደሚያጠናክር ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ኅብረት የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን የሰብዓዊ እርዳታና የአደጋ ስጋት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር  ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም ከአውሮፓ ኅብረት የሰብዓዊ እርዳታ ሥራዎች ምክትል ዳይሬክተር ጄነራል ማይክል ኮህለር ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በኢትዮጵያ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በግጭት ለተጎዱ አካባቢዎች እየተከናወነ በሚገኘው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ መክረዋል፡፡

ማይክል ኮህለር÷ ስምምነቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት በግጭት ለተጎዱ አካባቢዎች እያከናወነ ያለውን ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት አድንቀዋል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት በቀጣይ በኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሚያደርገውን የሰብዓዊ እርዳታ አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ማረጋገጣቸውን የኮሚሽኑ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ኅብረቱ በኢትዮጵያ ሊከሰቱ የሚችሉ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመከላከል በሚከናወኑ የአደጋ ስጋት ማስጠንቀቂያ ሥራዎች ላይ አስፈላጊውን ድጋፍ እደሚያደርግ ነው ያስገነዘቡት፡፡

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር  ኮሚሽን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ እንዲያቀርቡ በርካታ ጥረቶች እያደረገ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

በተመሳሳይ አምባሳደር ሽፈራው ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤይድ)  ምክትል ሃላፊ  ሚስተር ማቲው ጋር በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ ሁኔታዎች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

ዩ ኤስ ኤይድ ለኢትዮጵያ በሰብዓዊ እርዳታ፣ በዘላቂ ልማትና በአደጋ ስጋት ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ፈጣን ምላሽ ስራዎች ድጋፍ እንደሚያደርግ ምክትል ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

 

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.