Fana: At a Speed of Life!

የተለያዩ ሀገራት የፕሪቶሪያው ስምምነት ኢትዮጵያ ሰላሟ ተረጋግጦ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ኃላፊነት እንድትወጣ የሚያስችላት መሆኑን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ፣እስያ እና አውሮፓ ሀገራት የፕሪቶሪያው ስምምነት ኢትዮጵያ ሰላሟ ተረጋግጦ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ኃላፊነት እንድትወጣ የሚያስችላት መሆኑን ገለጹ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በወቅታዊ ሀገራዊ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም÷የአፍሪካ ፣እስያ እና አውሮፓ ሀገራት በፕሪቶሪያ የተፈረመው ግጭትን በዘላቂነት የማስቆም ስምምነት ኢትዮጵያ ሰላሟ ተረጋግጦ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ኃላፊነት እንድትወጣ የሚያስችላት ነው ማለታቸውን አብራርተዋል።

ይህም የሰባት ሀገራት አምባሳደሮች ለፕሬዚዳንት ሣህለወረቅ ዘውዴ የሹመት ደብዳቤያቸውን ሲያቀርቡ፣የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፣የጀርመን እና የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ነው ተብሏል።

የሹመት ደብዳቤያቸውን ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ያቀረቡት የሰባት ሀገራት አምባሳደሮች የሰላም ስምምነቱ ኢትዮጵያ ሰላቂ ሰላም የሚያመጣ እና ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ኃላፊነት እንድትወጣ እንደሚያስችላት መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የቻይናው አዲሱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ ወደ ኃላፊነትከመጡ ማግስት የመጀመሪያ የውጭ ሀገር ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያ መጀመራቸው ቻይና ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ልዩ ትኩረት እንደሚያሳይ አምባሳደር መለስ አብራርተዋል።

በተመሳሳይ የጀርመን እና ፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ጉብኝት በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ÷ ኢትዮጵያ በፈተና ባለፈችባቸው ዓመታት ጭምር ሁለቱ ሀገራት ያደረጉት የነበረውን የልማት ድጋፍ ሳያቋርጡ መቀጠላቸውን ያመላክታል ብለዋል፡፡

አሁንም ለሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚነት ሚኒስትሮች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል ነው ያሉት።

የሚሲዮን መሪዎች ስልጠና በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ÷ የስልጠናው ዓላማ ኢትዮጵያ ያለችበትን የድህረ ሰላም ስምምነት ወቅት በመገንዘብ ሀገራዊ፣ ቀጠናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የጂኦ ፖለቲካ አዝማሚያዎችን በመረዳት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በዲፕሎማሲው መስክ ማሥጠበቅ እንዲችሉ ማድረግ ነው ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.