Fana: At a Speed of Life!

ፋና ላምሮት ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ እንዲቀጥል መሰረታዊ ለውጥ እየተደረገ ነው – አቶ አድማሱ ዳምጠው

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ላምሮት በቴሌቪዥን የመዝናኛ ፕሮግራም ዘርፍ ከፍተኛ ተቀባይነት እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ እንዲቀጥል በቀጣይ መሰረታዊ ለውጥ አድርጎ ሊመጣ መሆኑን አቶ አድማሱ ዳምጠው አስታወቁ፡፡

ሦስተኛው ዙር የፋና ላምሮት የአሸናፊዎች አሸናፊ የድምጻውያን የፍጻሜ ውድድር የአዲስ አበባ የቴአትርና ባህል አዳራሽ እየተካሔደ ነው፡፡

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድማሱ ዳምጠው በውድድሩ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ፋና ላምሮት ቅቡልና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ እንዲቀጥል ዘመኑን የዋጀ ለውጥ አድርጎ እንደሚመጣ አስታውቀዋል፡፡

ይዘቱ ኅብረ ብሔራዊነትና አካታችነት እንዲኖረው ለማድረግ ከዕጩ ምልመላ ጀምሮ እስከ አቀራረብ ድረስ መሰረታዊ ለውጥ እንዲኖረው÷ ዘመናዊና የዓለም አቀፍ የጥበብ ውድድሮች መልክ ያለው የላምሮት ስቱዲዮ ግንባታ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

ፋና ላምሮት ስማቸውና ሥራቸው ለማይታወቁ ታዳጊ ሙያተኞች የመታያ እና የመታወቂያ መድረክ መሆኑን የገለጹት አቶ አድማሱ÷ ተቀባይቱና እና ተጽዕኖ ፈጣሪነቱ እንዲቀጥል በሚደረጉት የለውጥ ሥራዎች የዘርፉ ጠቢባን እገዛ እንዲጠናከር ጠይቀዋል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደ ፋና ላምሮት ያሉ የመዝናኛና የመማማሪያ መድረኮችን ሲያዘጋጅ ዓላማው÷ የሚኖርበትን ማኅበረሰብ ቁሳዊና ተፈጥሯዊ ፀጋዎች ውበታቸውን ጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ እንዲሁም የትናንቱ የስኬት መንገድ ለዛሬውና ለነገው ትውልድ ስንቅ እንዲሆን ከመፈለግ አንጻር ነው ብለዋል፡፡

ፕሮግራሙ ዕድሉን ላላገኙት መነሻ መድረክ፣ ለተረሱት ማስታወሻና ማሻገሪያ ድልድይ ሆኖ በርካታ ወጣት ድምጻውያንን ማፍራት የቻለ የውድድር ፕሮግራም መሆኑን ጠቅሰው÷ ዓላማና መዳረሻውም ትውልድ ላይ በመሥራት ለሙያው ክብር ከፍታ እገዛ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይ ከድምጻውያን ውድድር ባሻገር ብዙ ወጣቶችን በብዙ ቀለማት የሚያሳትፉ የጥበብ ሥራዎችን አካተን በልዩ አቀራረብ ለመምጣት እየሠራን ነው ብለዋል አቶ አድማሱ፡፡

ግባችን የብር ሽልማት ሳይሆን የሙያ ሽልማትና ዘርፉ በሙያም ሆነ በኢኮኖሚው በማያቋርጥ መልኩ እንዲያድግ ማድረግ ቢሆንም በየዙሩና በአሸናፊዎች አሸናፊ ሽልማቶችም ላይ ሙያውን የሚመጥን ለውጥ እናደርጋለን ነው ያሉት፡፡

ፋና ላምሮት ለጥበብ የተሰጠ ሥጦታ ስለሆነ ለሁለንተናዊ የጥበብ ዘርፍ ዕድገት ሁሉም ድርሻ ስላለው የሕዝብ አሳታፊነቱን ከነበረው የኤስ. ኤም. ኤስ. ተሳትፎ በላይ እንዲያድግ አዲስ የአሳታፊነት ስልት እንቀይሳለን ነው ያሉት፡፡

ፋና ላምሮት አድጎ እዚህ እንዲደርስ የማያቋርጥ ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.