ሕብረተሰቡ የጥምቀት እንግዶችን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት እንዲያስተናግድ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጥምቀት በዓል በሚከበርባቸው ቦታዎች የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንግዶችን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት እንዲያስተናግዱ የቱሪዝም ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ፡፡
በኢትዮጵያ የቱሪዝም ልማት ቁልፍ ሚና ያለውና በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የጥምቀት በዓል ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ÷ ተቀዛቅዞ የነበረውን ቱሪዝም እንዲነቃቃ ለማድረግ እና በዓሉን በልዩ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን ሚኒስቴሩአስታውቋል፡፡
የጥምቀት በዓል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተለይም አዲስ አበባን ጨምሮ በጎንደር፣ በዝዋይ እና በምንጃር ኢራንቡቲ በድምቀት የሚከበር መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
የጥምቀት በዓል በሚከበርባቸው ቦታዎች ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች በዓሉን ለመታደም ስለሚገኙ÷ ሕብረተሰቡ ኢትዮጵያዊ እንግዳተቀባይነት ባህሉን ተላብሶ ፍፁም ጨዋነት በተሞላ መንፈስ እንግዶቹን በጥሩ ሁኔታ ለማስተናገድ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ሲል ሚኒስቴሩ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
በዓሉ የሰላም፣ የጤና፣ የፍቅር እና የአንድነት እንዲሆን ሚኒስቴሩ መልካም ምኞቱ ገልጿል፡፡