የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ የጥምቀት በዓል ተከብሮ እስኪጠናቀቅ ሞተር ብስክሌት ማሽከርከር ተከለከለ

By Alemayehu Geremew

January 16, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የጥምቀት በዓል ምክንያት በማድረግ ከዛሬ ጥር 8 ቀን 6 ሠዓት ጀምሮ እስከ ሐሙስ ጥር 11 ቀን 2015 ዓ.ም አመሻሽ 12 ሠዓት ድረስ ሞተር ብስክሌትን ማሽከርከር ፍጹም የተከለከለ መሆኑን የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡

ክልከላው የሚመለከተው የፀጥታ እና የትራፊክ ቁጥጥር ሥራ አካላት ከሚጠቀሙባቸው ሞተር ብስክሌቶች ውጪ በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱትን ባለሁለት እግር ሞተር ብስክሌቶች በሙሉ ነው፡፡

የሞተር ብስክሌት ባለንብረቶችም ሆኑ አሽከርካሪዎች ይሄንኑ ክልከላ መሰረት በማድረግ እስከ ተጠቀሰው ቀን ድረስ በትዕግስት እንዲጠብቁ ኤጀንሲው አሳስቧል፡፡

ይህንን መልዕክት በሚተላለፉ አካላት ላይም ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ ነው ኤጄንሲው ያስታወቀው፡፡