ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2050 የካርበን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ ግብ አስቀምጣ እየሰራች ነው -ጠ/ሚ ዐቢይ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2050 የካርበን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ ግብ አስቀምጣ በትኩረት እየሰራች ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በሚመክረው15ኛው የአቡ ዳቢ ዓለም አቀፍ “ሰስቴኔቢሊቲ” ጉባዔ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ በርካታ ስራዎች እያከናወነች መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የታዳሽ ሃይሎች ባለቤት መሆኗን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በአሁኑ ወቅት ከውሃ፣ ከነፋስ፣ ከጸሃይ እና ከእንፏሎት ሃይል በማመንጨት ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።
ከዚህ እምቅ ሃብት በመነሳትም ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2050 የካርበን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ ግብ አስቀምጣ በትኩረት እየሰራች ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ባለፉት አራት ዓመታት 25 ሚሊየን ዜጎችን በማሳተፍ 25 ቢሊየን ችግኞች መትከል መቻሏን አንስተዋል፡፡
ይህም 64 ሚሊየን በጋዝ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ለአንድ ዓመት ያህል ጊዜ ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን የተበከለ አየር እንደማስቀረት ይቆጠራል ነው ያሉት፡፡