Fana: At a Speed of Life!

በሐረሪ ክልል የከተራና የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል የከተራና የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ

በሐረሪ ክልል ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ዋደራ እንደገለፁት÷ በክልሉ የከተራና የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ተጠናቋል።

በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅም የክልሉ ፖሊስ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በቂ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቀው ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።

በዓሉ ካለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅም ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሰላም አደረጃጀቶች፣ ወጣቶችና ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሰፊ ውይይት መደረጉን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅትም በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የተጠናከረ ፍተሻዎችና ጥበቃዎች እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በአካባቢው በብሔርና በሀይማኖት መካከል ችግር እንዲፈጠር የሚፈልጉ አካላት ስለመኖራቸው ያነሱት  ኃላፊው÷ ህዝቡ በፀጥታ ስራው ላይ እያደረገ የሚገኘውን የላቀ አስተዋጽኦ በማጠናከር የእነዚህን አካላት ፍላጎት እንዳይሳካ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ እየተስተዋለ ለሚገኘው አንፃራዊ ሰላም የህዝቡ ሚና የላቀ መሆኑን መጠቆማቸውንም ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነወ መረጃ ያመላክታል፡፡

በቀጣይም የክልሉን ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ሰላም ወዳዱ ህዝብ እያደረገ የሚገኘውን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.