Fana: At a Speed of Life!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወጪ የሚገነባውን የለሚ አደባባይ ግንባታ አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወጪ የሚገነባውን የለሚ አደባባይ ግንባታ አስጀምረዋል።

ከንቲባዋ በዚሁ ወቅት ÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ተጨማሪ መስቀል አደባባዮች ለከተማዋ ያስፈልጓታል” ባሉት መሰረት ቃላቸውን ፈፅመን ለዚህ ፕሮጀክት ዛሬ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠናል ብለዋል፡፡

ቦታው የተመረጠበት ዋነኛ ምክንያትም አዲስ አፍሪካ አለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እዚህ አካባቢ እየተገነባ በመሆኑ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች አካባቢው ተጨማሪ አገልግሎቶችና ተያይዘው የሚመጡ ስፍራዎች የሚያስፈልጉት መሆኑንም አውስተዋል፡፡

ከተማችንን ልንቀይር የምንችለው የዘመነ አሰራርና አስተሳሰብ በመያዝ ፤ የግሉን ሴክተር በማሳተፍ የመንግስትን ክፍተት በመሙላት እና በአጭር ጊዜ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ 14ሺህ 400 ካሬሜትር ላይ የሚያርፍ ሲሆን÷ የህዝብ ስፍራ አደባባይ፣ የመኪና ማቆምያ፣ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ ጂምናዝየሞችን፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ የህዝብ መሰባሰቢያ ስፍራ፣ የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ፣ የሰርግና ሌሎች አገልግሎቶች የሚውል መናፈሻ፣ የገበያ ማዕከል፣ የቢሮ አገልግሎት የሚሰጡ ቦታዎች፣ መጽሀፍት የማንበቢያ ስፍራና የመሳሰሉት ይኖሩታል ተብሏል፡፡

ይህ ፕሮጀክት በግንባታው ወቅት እስከ 1 ሺህ 100 ያህል ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥርና በቀጣይ በቋሚነት ለ400 ዜጎች የስራ ቦታቸው የሚሆን ነው መባሉን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ስራው በ10 ወራት ተገንብቶ የሚጠናቀቅ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.