Fana: At a Speed of Life!

ለጥምቀት በዓል ወደ ጎንደር ለሚመጡ እንግዶች የተሳለጠ አገልግሎት እንዲያገኙ ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎንደር ከተማ ለጥምቀት በዓል ለሚመጡ እንግዶች የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ማድረጋቸውን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ገለጹ፡፡

በኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ምዕራብ ሪጅን የኦፕሬሽን ዳይሬክተር ወርቃለማሁ ዳኛቸው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ እንግዶች በከተማዋ በሚኖራቸው ቆይታ የኔትወርክ መቆራረጥ እንዳያጋጥማቸው ዝግጅት ተደርጓል።

በዚህም÷ ያሉት ሳይቶች ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ፣ 15 ማስፋፊያ የሚያስፈልጋቸው ሳይቶች ተለይተው የኔትወርክ ካርድ ማስፋፊያ በማድረግ የማስተናገድ አቅማቸውን ማሳደግ እና በጥምቀተ ባሕሩ አካባቢ አንድ የሞባይል አንቴና መተከሉን አብራርተዋል፡፡

በጥምቀተ ባሕሩ ኢትዮ ቴሌኮም ነጻ የዋይፋይ አገልግሎት ማዘጋጀቱንም ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጎንደር ዲስትሪክት ዳይሬክተር ሞገስ አበራ÷ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዳይቋረጥ መስመሮችን የመከታተልና የመጠገን ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

በድንገት የኃይል መቋረጥ ቢከሰት በፍጥነት ጥገና የሚያከናውኑ ቡድኖች ዝግጁ መሆናቸውን የሥራ ኃላፊዎቹ አረጋግጠዋል፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ በለጠ ፈንቴ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የሚያቀርቡት ምርትና አገልግሎት ጤንነቱ ስለመጠበቁ ቁጥጥርና ክትትል መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

በጥምቀት በዓል የሰዎች እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ድንገተኛ አደጋዎች ቢከሰቱ የጤና ተቋማት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በተጨማሪም አስፈላጊውን የሕክምና ቁሳቁስና ባለሙያዎች ያካተቱ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና አገልግሎት መስጫ ተንቀሳቃሽ ማዕከላት መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት፡፡

የጎንደር ከተማ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ቻላቸው ዳኜው እንዳሉት÷ በጥምቀት በዓል ወቅት ከ750 ሺህ እስከ 1 ሚሊየን ጎብኚ ወደ ጎንደር እንደሚመጣ ይጠበቃል።

ለዚህም ከ400 በላይ ሆቴሎች እና ድንኳን የሚጣልባቸው ቦታዎች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው÷ እንደ እንግዶች አቅም የማረፊያ፣ የምግብና መጠጥ መሸመቻ አማራጭ መሰናዳቱን አስገንዝበዋል።

በሰሞነ ጥምቀት ከቱሪዝም እስከ 2 ቢሊየን ብር ገቢ እንደሚያገኝም አመላክተዋል፡፡

የዘንድሮው የጥምቀት በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ በጎንደር በልዩ ሁኔታ ስለሚከበር ጎብኚዎች እንዲገኙ የቱሪዝም ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን ገልፀው፥ በዓሉ በሚከበርባቸው ቦታዎች ምዕመኑ እና የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ጭምር ሰላማዊ በሆነ መንገድ የበዓሉ ታዳሚዎች አክብረው እንዲመለሱ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.