Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ በቅርቡ ለተሾሙት አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤ ሰጡ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ በቅርቡ ለተሾሙት 14 ባለሙሉ ሥልጣን አምሳደሮችና 7 አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤ ሰጡ፡፡

የሹመት ደብዳቤ የመስጠት መርሐ -ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተከናውኗል።

ፕሬዚዳንቷ በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ ሀገራት ኢትዮጵያን ማገልገል ትልቅ ዕድል እንደሆነ ጠቅሰው ፥ ተሿሚ አምባሳደሮች ዕምነትንና ሰርቶ ማሳመንን መርኅ አድርገው ሊሰሩ ይገባል ማለታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡

ስክነትና ጠንካራነትን በመላበስ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በማስከበር ረገድ ከተሿሚ አምባሳደሮች በርካታ ሥራዎች እንደሚጠበቁም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ሁለት የፈተና ዓመታትን ካሳለፈች በኋላ ወደ ተሥፋ እየተመለሰች ነውም ብለዋል፡፡

ቀጣይነት እንዲኖረውም አምባሳደሮች ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ፥ ሀገር ስትፈተን አብሮ የተጎዳው ዲፕሎማሲ አሁን ላይ እየተነቃቃ እና ግንኙነቶች እየተሻሻሉ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

ችግሮች አልፈው ሠላምን የማፅናት፣ የተጎዱ አካባቢዎችና ተቋማትን የመገንባት እንዲሁም የተፈናቀሉ ዜጎችን የማቋቋም ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።

ሀገርን የመጠበቅ ሥራ ችግሮች ሲፈጠሩ ብቻ ሳይሆን ሁሌም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

ተደማጭና ተመራጭ፣ ብሔራዊ ጥቅሟ የተረጋገጠ ሀገር እንድትኖረን ተሿሚ አምባሳደሮች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አቶ ደመቀ መኮንን አሳስበዋል፡፡

ተሿሚ አምባሳደሮች በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መዓዛ አሸናፊ አማካኝነት የኢትየጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ በመንግሥታት መካከል ግንኙነቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በትጋት እንደሚሰሩ ቃለ-መሃላ ፈፅመዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.