Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ ሚ ዐቢይ በአቡ ዳቢ በግንባታ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአቡ ዳቢ በግንባታ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጎብኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ ዛሬ በአቡዳቢ በመሠራት ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጎብኝቻለሁ ብለዋል።

ለመስሪያ ቦታም 17 ሺህ 682 ካሬ ሜትር መሬት ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች መንግሥት የተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ስም ምስጋና ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ለጊዜው መገልገያ የሚሆነው ቤተ ክርስቲያን እየተጠናቀቀ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የጥምቀት በዓል በቦታው እንዲከበር የሚቻለው ሁሉ እንደሚደረግ ከሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ቃል መገባቱንም አስረድተዋል፡፡

“ይሄንን መሰል ቦታዎች የታሪክና የዲፕሎማሲያችን ትእምርቶች ናቸው፤ እነርሱ ለእኛ ይሄንን ሲያደርጉ፣ እኛ ለገዛ ወገኖቻችን ከዚህ በላይ እንድናደርግ ትምህርት ይሆነናል” ሲሉም ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.