Fana: At a Speed of Life!

ለከተራና ጥምቀት በዓላት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ግብረ ኃይሉ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች ጋር ተወያይቷል፡፡

ውይይቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች ከፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ጋር በመተባበርና በመናበብ በዓሉን ሰላማዊ እንዲሆን ለማስቻል ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በመድረኩ የከተራና የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉ ተብራርቷል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል÷ የከተራና የጥምቀት በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡

ግብረ ኃይሉ በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ለማድረግ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች በርካታ የፀጥታ አካላት ማሰማራቱን ገልጸው÷ በታቦታት ማደሪያ ስፍራዎችና በርካታ የበዓሉ ታዳሚዎች በሚገኙበት አካባቢ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

የሀገርን ሰላም ለማደናቀፍ የሚፈልጉ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ሕዝብ የሚሰበሰብበትን አጋጣሚ ተጠቅመው ሰላም ሊያውኩ ስለሚችሉ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የሃይማኖት አባቶች የአብሮነትና ሰላም መገለጫ የሆነውን በዓል ለፖለቲካ ትርፋቸው ለማዋል የሚሰሩ አካላትን በመከላከል ረገድ ከጸጥታ ተቋማት አባላት ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው÷በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተው የጋራ አቋም መያዛቸውን ገልፀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ጥምቀት ሃይማኖታዊና የሰላም በዓል መሆኑን የተናገሩት አባቶቹ÷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ እምነት ተከታዮች በዓሉ በሰላም እንዲከበር ኃላፊነት ወስደው የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የጥምቀት በዓል ከኢትዮጵያ ባለፈ የዓለም ቅርስ መሆኑን ጠቅሰው÷ የክብረ በዓሉ ተሳተፊዎች ይህን በሚመጥን መልኩ በሰላም እንዲከበር ሚናቸውን በመወጣት የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ ለዓለም ማስተዋወቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.