Fana: At a Speed of Life!

ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው ከአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ዶ/ር አኔት ዌበር ከተመራው የልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል፡፡
 
በውይይታቸውም በኢትዮጵያና በአውሮፓ ህብረት መካካል ስለሚኖረው ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትብብር ዙሪያ መክረዋል፡፡
 
ወ/ሮ ሰመሪታ የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት አጋር መሆኑን ጠቅሰው÷ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በሰሜን ኢትዮጵያ በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት ገለጻ አድርገዋል፡፡
 
የሁለተኛውን የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ በማድረግ የሀገሪቱን ልማትና እድገት ለማፋጠን እየተደረጉ ስላሉ ጥረቶችም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
 
በግጭት የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን በዘላቂነት ለማቋቋምና የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ከፍተኛ ሃብት ማሰባሰብ እንደሚያስፍልግ አስረድተዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓ ህብረት ያሉ ዘላቂ የልማት አጋሮች በዚህ ረገድ የሚያበረክቱትን የሰብዓዊ እርዳታና የልማት ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
 
የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ዶ/ር አኔት ዌበር በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ምስራቅ አፍሪካን ለማረጋጋትና ቀጠናዊ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር አስተዋጽኦ ያላት ሀገር መሆኗን አውስተዋል፡፡
 
በኢትጵያ ሰላም መስፈኑ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያለውን ሁለንተናዊ ትብብር ለማጠናከር በጣም አስፈላጊ እንደሆነ መጠቆማቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
የአውሮፓ ህብረት ከኢትጵያ ጋር ያለውን ዘርፈ ብዙ ትብብር ወደ ነበረበት ለመመለስና ብሎም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በቀጣይነትም ተከታታይ ውይይት በማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ ላማድረግ በህብረቱ በኩል ቁርጠኝነት እንዳለ አረጋግጠዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.