Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
 
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
 
እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ!
 
የጥምቀት በዓል ብዙ ትርጉሞችን ይዞ የሚከበር በዓል ነው፡፡ በአንድ በኩል ለክርስቲያኖች ትኅትናን የሚማሩበት፣በእግዚአብሔር ማመናቸውን የሚያውጁበት፣ ንስሐና ድኅነት የሚያገኙበት ምልክት ሆኖ ያገለግላል፡፡ በሌላ በኩል እንደ ሀገር የጥምቀት ክብረ በዓል መልከ ብዙ የሆንን ኢትዮጵያውያን ኅብር ፈጥረን የምንደምቅበት በመሆኑ ታላቅ ቦታ ሰጥተን እናከብረዋለን፡፡
 
በዓለ ጥምቀትና ትኅትና ተነጣጥለው የሚታዩ ጉዳዮች አይደሉም፡፡ ምክንያቱም ጥምቀት ፈጣሪ በፍጡር፣ አምላክ በሰው፣ ጌታ በአገልጋዩ የተጠመቀበት እለት ነውና። ከነበረበት ከፍታ ወርዶ ከሰው የተስተካከለበት፣ ከቆመበት የጌትነት ስፍራ ዝቅ ብሎ ትኅትናን ያሳየበት፣ ትእቢትን ሽሮ ለሰው ልጆች ትኅትናን ያስተማረበት አጋጣሚ ነው – ሥርዓተ ጥምቀቱ። በሥርዓተ ጥምቀቱ አጥማቂው ዮሐንስም ያሳየው ትኅትና እንዲሁ በምሳሌነት ይጠቀሳል፡፡
 
ፈጣሪው የሰጠውን ክብር እንደሚገባው ቆጥሮ በተዓብዮ ሳይታጠር፤ ‘እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን?’ ብሎ ማከላከሉ የመከበር ምሥጢሩ ትኅትና እንደሆነ፣ የኃይልና የብርታት ቁልፍ ታዛዥነት ውስጥ እንዳለ፣ የበላይነት መገኛውም ወደታች ወረዶ እያገለገሉ ጽድቅን መፈጸም እንደሆነ ያስተምረናል።
 
ሰዎች ከላይ የሆኑ ሲመስላቸው የታቹን የማያዩና የገዘፉ ሲመስላቸው በቅንነት ጎንበስ የማይሉ ከሆነ እነሱ የጥምቀቱ ትርጉም አልገባቸው። ትኅትናን ንቀው ትዕቢትን የመረጡ፣ ዝቅ ማለት ከብዷቸው ራሳቸውን ከፍ ከፍ ያደረጉ፣ ቅንነትን ጠልተው ግፍ መሥራት የወደዱ መጨረሻቸው ዕድገት ሳይሆን ቁልቁለት፣ ክብር ሳይሆን ውርደት መሆኑን በብዙ አጋጣሚዎች ዓለም አሳይታናለች።
 
በተቃራኒው የተሰጣቸውን ኃይል ለመልካም ዓላማ የተጠቀሙ ዘወትር ሥማቸው በጥሩ ሲነሣ ይኖራሉ። እንደ ሙሴ ያሉት የተሰጣቸውን በትር ባሕር ከፍለው ሕዝብን ወደ ተስፋ ሲያሻግሩ፤ እንደ ጎልያድ ያሉት ከሰው ሁሉ በላይ መግዘፋቸውን ለበደል ተጠቅመውታል፤ በዚህም ምክንያት ሙሴዌች ሲወደሱ ጎልያዶች በቀላሉ በጠጠር ወድቀዋል። ዓይናችንን ገልጠን ብንመለከት በዙሪያችን ከፍታቸውን ለክፋት፣ ኃይላቸውን ለጭቆና በመጠቀማቸው አሳዛኝ ውድቀት የገጠማቸው ጎልያዶችን በአቅራቢያችን እናገኛለን። ተመሳሳዩ ዕጣ እንዳይገጥመን ሁላችንም ትኅትናና መልካምነትን ገንዘባችን ልናደርግ ይገባል።
 
ሌላኛው የጥምቀት ምሳሌ የመዳንና የንስሐ ምልክት መሆኑ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ፈለገ ዮርዳኖስ ከመውረዱ በፊት በኃጢአት የተሸፈነውን አዳም የኃጢአቴ ልብሱን ከላዩ ላይ ሊጥልለት የሞከረ አልነበረም። ጌታ ኢየሱስ በማዕከለ ዮርዳኖስ የመቆሙ ምክንያት የአዳምን ውርደት ለመቀበል፣ ኃጢአቱን ወስዶ ከመከራው ለማዳን፣ የሚነትበውን ልብስ ጥሎ በማይነትብ ዘላለማዊ ልብስ ለመተካት ነበር። በየዓመቱ ጥምቀቱን የምናከብረውም ከፊት-ቀድሞ ከመከራ የታደገን ክርስቶስን እያሰብን ነው።
 
ዛሬ የምናያቸውና የምንረማመድባቸው መንገዶች በአንድ ወቅት ጢሻ የነበሩና በፊት ቀደሞች መሥመር የወጣላቸው ናቸው። ዛሬ የሠለጠኑ ሀገሮች የሥልጣኔ ከፍታ ላይ የደረሱት በአንድ ወቅት ፊት አውራሪዎቻቸው በመከራ ውስጥ አልፈው፣ ችግርና ፈተናውን ተሻግረው መሠረት ስላኖሩላቸው እንጂ አዲስ ተዓምር ተፈጥሮላቸው አይደለም። ድኅነት፣ መታደስና ብልጽግና የሚመጣው ፊት ቀዳሚዎች ችግርና መከራውን ተጋፍጠው መንገድ ማስመር ሲችሉ ብቻ ነው።
 
እኛ የዛሬው ትውልዶች ለሀገራችን ፊት ቀዳሚዎቿ እንደሆንን ማመን ይገባናል። እኛ መከራዋን ሳንቀበል ለኢትዮጵያችን ምቾት፣ ዝቅታውን ሳናይ ለሀገራችን ከፍታ፣ ጭለማውን ሳንጎበኝ ለልጅ ልጆቻችን ብርሃን እንደማይመጣ ማወቅ አለብን። ሀገራችን በድህነትና እርዛት የጠየመ ፊቷን፣
በኋላቀርነትና በጉስቁልና ያደፈ ልብሷን እኛ ወስደን በአዲስና በሚያበራ የመተካት ኃላፊነት እያንዳንዳችን ትከሻ ላይ ወድቋል። ኃላፊነታችንን በአግባቡ ከተወጣን የማናፍርባትን ሀገር፣ የሰለጠነች ኢትዮጵያን፣ የምንኮራበት ታሪክን ለልጅ ልጆቻችን ማስተላለፍ እንችላለን። ቅድመ አያቶቻችን ዋጋ ከፍለው በማለፋቸው ዛሬ የምንኮራባቸውን ሀገራዊ እሴቶች እንዳገኘን ሁሉ፤ እኛም ለመጪው ትውልድ ተመሳሳዩን ማድረግ ይጠበቅብናል።
 
ውድ የሀገሬ ሕዝቦች፣
 
በዓለ ጥምቀቱ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ከሃይማኖታዊ ክብረ በዓልነቱ በዘለለ ባህላዊ እሴቶቻችን የሚስተናገዱበት በዓል ጭምር ነው። ከጎንደር እስከ ሐረር፣ ከመቀሌ እስከ ባሌ፣ ከመተማ እስከ ጅማ በየስፍራው ኢትዮጵያውያን ወደ አደባባይ ይወጣሉ። አያሌዎች ዘመድ ለመጠየቅ ከቦታ ቦታ ይተምማሉ። ማኅበራዊ ኑሯችን የሚደምቅበት፣ በልዩ ልዩ አልባሳት የምናጌጥበት፣ ልዩ ልዩ ኅብረ ዜማዎችን የምንሰማበት ዕለት ነው። ጥምቀት የአደባባይ የባህል ሙዝየማችን ነው።
 
ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ብሔሮች፣ ቋንቋዎች፣ አለባበሶች፣ የፀጉር አሠራሮች፣ ዜማዎች ወዘተ አሏት ብሎ ለሚጠይቅ፤ የጥምቀትን በዓል ተመልከት! ብሎ መመለስ ይቻላል። በዚህ ምክንያት ከዓለም በተለየ ጥምቀትን የእኛ ቅርስ ማድረግ ችለናል። ይሄንን ልምድ በሌሎች ዘርፎችም ልንደግመው ይገባል።
 
ዴሞክራሲን በእኛው ቁመትና ወርድ ሰፍተን ካበጃጀነው፣ ቴክኖሎጂዎችን ኢትዮጵያዊ ለዛ ሰጥተን ከሠራነው፣ በኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች እኛን የሚመስሉ እሴትና ወረቶችን ካዳበርን በርግጥም ዓለም ፊቱን ወደእኛ ማድረጉ አይቀርም። ዛሬ ባሕረ ዮርዳኖስ ከሚገኝበት ሀገረ እስራኤል ጨምሮ ከመላው ዓለም ጥምቀትን ለመታደም በየዓመቱ ቱሪስቶች ወደ እኛ ይመጣሉ። የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎችን የሚስብ ታላቅ ቀን በመሆኑ ጥምቀት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም እናገኝበታለን።
 
ከዚሁ ጋር ተያይዞ አንድ ማወቅ ያለብን እውነት የኢትዮጵያ በዓላት የኢትዮጵያውያን ሁሉ በዓላት መሆናቸው ነው። በእምነቱ ብናምንም ባናምንም፣ በዓሉ ግን በዜግነት የሁላችንም ነው። የጥምቀትም፣ የዒድ አል ፈጥርም፣ የፋሲካም፣ የዒድ አልአድሐም፣ የገናም፣ የመውሊድም በዓል የሁላችንም ናቸው። የሀገራችን ሀብት የወገኖቻችን ደስታ ናቸውና እንኮራባቸዋለን። ሁላችንም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳና እና ማኅበራዊ ጥቅም እናገኝባቸዋለን። በተለይ እንደ ጥምቀትና አረፋ ያሉ የአደባባይ በዓሎቻችንን በአማረና በደመቀ ሁኔታ እንዲከበሩ ሁላችንም እኩል ልንደክም ይገባል።
 
መቼም ቢሆን፣ ጥምቀት ተስተጓጉሎ አረፋ፤ አረፋ ተስተጓጉሎ ጥምቀት አይሠምርምና። ለሁላችንም ደስታ እያንዳንዳችን የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ይገባናል። በዓሉ በሰላም፣ በድምቀትና በክብር እንዲከናወን የምትተጉ ሁሉ ምስጋና ይገባችኋል።
በድጋሚ፣መልካም የከተራና የጥምቀት በዓል እንዲሆን እመኛለሁ።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
 
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
 
ጥር 10፣ 2015 ዓ.ም
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.