የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ሁሉም ዜጋ የበኩሉን እንዲወጣ መንግስት ጥሪ አቀረበ
አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት የጥምቀት በዓል በሰላምና በድምቀት እንዲከበር ሁሉም ዜጋ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅና ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በጋራ በመሆን ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ሚኒስትሩ፥ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የሚከበሩት የከተራ፣ ጥምቀትና ቃና ዘገሊላ በዓላት በመላ ሀገሪቱ በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበሩ ጠቅሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋብ ማለቱና የተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም በዓላቱ ይበልጥ ደምቀው እንዲከበሩና ከመንፈሳዊ ሥርዓቱ ባሻገር ለኢትዮጵያውያን የእርስ በርስ ግንኙነት፣ ለቱሪዝም መስህብነት እና ያለንን እሴቶች ለዓለም ማህበረሰብ በማሳየት ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው ነው የተናገሩት።
ዛሬ በአዲስ አበባ ታቦታቱ ከመቅደሳቸው ወጥተው ጃንሜዳን ጨምሮ በተዘጋጁላቸው የጥምቀተ-ባህር ማረፊያ ስፍራዎች እንደሚያቀኑ ጠቁመዋል።
እነዚህን አካባቢዎች ምቹ በማድረግ ከእምነቱ ተከታዮች ባሻገር የሁሉም እምነት ተከታዮች በአብሮነትና መከባበር አካባቢዎቹን ሲያጸዱና ለበዓሉ ሲያዘጋጁ ቆይተዋል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም፥ በዓሉ በመላው የሀገሪቱ ክፍል በሰላም እንዲከበር በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚገኘው የጸጥታ መዋቅር እንዲሁም በፌዴራል ደረጃም የጸጥታና የደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል፡፡
በበዓሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የምህበረሰብ ክፍል በአንድ ቦታ መሰብሰቡን እንደምቹ አጋጣሚ ተጠቅሞ ሰላምን የሚያውኩና ከበዓሉ ኃይማኖታዊ አስተምህሮ ባፈነገጠ መልኩ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በማጋለጥ ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡
ሁሉም የጸጥታ ኃይሎች በተሟላ ዝግጁነትና ብቃት ላይ መሆናቸውንም ነው ያነሱት፡፡
በዚህም ህብረተሰቡ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን አካባቢያቸውን እንዲጠብቁና አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከቱ በመጠቆም በዓሉ በሰላም እንዲከበር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተጨማሪም የጤና ሚኒስቴር ባወጣው የኮቪድ-19 መመሪያ መሰረት እራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን ከወረርሽኙ መጠበቅ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡
በመሰረት አወቀ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!