Fana: At a Speed of Life!

የሸኔ እንቅስቃሴ የታየባቸው አካባቢዎችን ወደ ቀደመ ሁኔታቸው ለመመለስ በቅንጅት እየተሰራ ነው – ዶ/ር ለገሰ ቱሉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የሸኔ እንቅስቃሴ የታየባቸውን አካባቢዎች ወደ ቀደመ ሁኔታቸው ለመመለስ የፌዴራል እና የክልሉ መንግስት የጸጥታ ሃይሎች ሁሉንም አይነት እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፥ የሽብር ቡድኑ ሸኔ በኦሮሚያ እና አጎራባች አካባቢዎች ህገ ወጥ ታጣቂዎችን በማሰማራት ከሌሎች የስጋት ሃይሎች ጋር ጥምረት በመፍጠር በንጹሃን ዜጎች ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡

ሸኔ በአሮሞ ሕዝብ ስም የሚንቀሳቀስ ቢሆንም በዋነኛነት የሚያጠቃው የኦሮሞን ህዝብ ነው፤ የሽብር ቡድኑን የሚደግፉት ደግሞ ኢትዮጵያን ማዳከም የሚፈልጉ ሃይሎች ናቸው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ሸኔ የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም እና ፍላጎት መሰረት ያደረገ አላማም ሆነ ምክንያት የለውም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የሽብር ቡድኑን ስጋት ለመቀልበስም የተቀናጀ ሁሉን አቀፍ እርምጃ እየተሰወደ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ሲደረጉ የነበሩት የመንግስት የፖለቲካ እና የሰላም አማራጮች የመጀመሪያ አማራጭ መሆናቸውንም አስታውሰዋል፡፡

ሸኔ የሰላም ጥሪውን ተቀበሎ እኩይ ተግባሩን እንዲያቆም እና የኦሮሞ ወጣት እልቂት ማብቂያ እንዲያገኝም መላው ሕዝብ ግፊት ማድርግ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

መንግስት በየደረጃው ካሉ የመንግስት አካላት ጋር በየቀበሌው የሰላም ውይይት እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሽብር ቡድኑ የተቀላቀሉ ወጣቶች በሰላም ለመንግስት እጃቸውን እንዲሰጡ እና የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ህብረተሰቡን እንዲቀላቀሉ የቅድሚያ ቅድሚ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም በርካታ ወጣቶች ጥሪውን እየተቀበሉ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

እነዚህ ሁኔታዎች ባልተቻሉባቸው አካባቢዎችም የሽብር ቡድኑ የሚያደርሰውን ሁሉን አቀፍ ጉዳት ለመቀልበስ መንግስት የሃይል እርምጅ እየወሰደ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

በዚህም በቡድኑ ታጣቂዎች፣ አባላት እና የሎጂስቲክ አቅራቢዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት፡፡

እነዚህ አካባቢዎች ከሸኔ ወረራ ነጻ በመሆን ዳግም እንዲደራጁ እና መሰረታዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙም በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.