Fana: At a Speed of Life!

በሀገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሃይማኖት መቻቻልን ማስፈን ያስፈልጋል – ከንቲባ አዳነች አበቤ

አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ብሎም በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን የሃይማኖት መቻቻልን፣ ፍፁም ትህትና እና አገልጋይነትን ማስፈን ያስፈልጋል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

ከንቲባ አዳነች በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በተከበረው የጥምቀት በዓል በመገኘት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም፥ “የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ አምላክ ሆኖ ሳለ በፍፁም ትህትና በሰው እጅ የተጠመቀበትን ዕለት ለማስታወስ የሚደረግ በዓል” ሲሉ አንስተዋል፡፡

በዓሉ ሃይማኖታዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በዝማሬ፣ በአምልኮ፣ በአብሮነት እና በአገልጋይነት ከትላንት ጀምሮ በመዲናዋ እየተከበረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡን ያነሱት ከንቲባዋ፥ በዚህም በዓሉ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮቸ በተጨማሪ የመላው ኢትዮጵያውን በዓል ሆኗል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደ ጥምቀት ያሉ ህዝባዊ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ሲሰራ መቆየቱን እና ለወደፊትም እንደሚሰራ ከንቲባዋ አረጋግጠዋል፡፡

የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር አስተዋፅዖ ላደረጉት የከተማው ነዋሪዎች እና የከተማዋ የፀጥታ አካላት ከንቲባዋ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.