Fana: At a Speed of Life!

በሦስት የእሳት አደጋዎች 6 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ወደመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ እና አካባቢዋ በተከሰቱ ሦስት የእሳት አደጋዎች 6 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በሦስቱም አደጋዎች በሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱ እና ከ900 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ማዳን መቻሉ ተገልጿል፡፡

በኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት÷ ትናንት ከአመሻሹ 11፡15 እስከ ሌሊት 10፡ 05 ባለው ጊዜ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ሦስት የእሳት አደጋዎች

ምክንያት 6 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የተገመተ ንብረት ወድሟል፡፡

ትናንት ከአመሻሹ 11፡15 ላይ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድአርባ አንድ ኢየሱስ አካባቢ በምግብ ማብሰያ ክፍል ውስጥ ከኤሌክትሪክ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የእሳት አደጋ መከሰቱን ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም ትናንት ከአመሻሹ 12፡15 ላይ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 በጉለሌ ፋና ትምህርት ቤት አካባቢ በመኖሪያ ቤት ውስጥ ለአገልግሎት ተለኩሶ በነበረ ሻማ ምክንያት አደጋ መከሰቱን ነው ያብራሩት፡፡

ሦስተኛው በሸገር ከተማ አስተዳደር ቡራዩ ጉጄ አካባቢ ሌሊት 10፡05 ገደማ በንግድ ሱቆች ላይ የተከተሰተ የእሳት አደጋ ነው፡፡ የተለያየ አገልግሎት የሚሰጡ 18 ሱቆች መጎዳታቸውንም ነው አቶ ንጋቱ የተናገሩት፡፡

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ባደረጉት ርብርብ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረግ መቻሉንም ነው የገለጹት፡፡

ሦስቱንም አደጋዎች ለመቆጣጠር 71 የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች፣ ስምንት የአደጋ መቆጣጠር ማሽነሪዎች እና ሦስት አንቡላንስ መሠማራቱ ተገልጿል፡፡

ህብረተሰቡ ከኮሚሽኑ የሚተላለፉ መረጃዎችን እና መልዕክቶችን በመተግበር እራሱን ከአደጋ እንዲጠብቅ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.