የሀገር ውስጥ ዜና

በኮሮና ቫይረስ በሽታ ምክንያት በኢትዮጵያ ሁለተኛው ሞት መመዝገቡን የጤና ሚኒስቴር ገለፀ

By Meseret Demissu

April 05, 2020

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኮሮና ቫይረስ በሽታ ምክንያት በኢትዮጵያ በዛሬው እለት ሁለተኛ ሰው ህይወት ማለፉን የጤና ሚኒስቴር ገለፀ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደገለፁት፥ ታማሚው በለይቶ ማቆያ ከመጋቢት 24 ጀምሮ ህክምና ሲደረግላቸው የነበርና ከገቡበት ቀን ጀምሮ በጽኑ ህሙማን ክፍል ክትትል ላይ የነበሩ ናቸው።

ታማሚው ዛሬ ከምሽቱ 12 ሰዓት ህይወታቸው እንዳለፈም ገልጸዋል።

ሚኒስትሯ በዚህም የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በራሳቸውና በጤና ሚንስቴር ስም በመግለፅ ለቤተሰቦቻቸው እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ልባዊ መጽናናትን ተመኝተዋል።

የመጀመረያው ሞት ዛሬ ጥዋት ላይ የተመዘገበ ሲሆን፥ ህይወታቸውን ያጡት የ60 ዓመት ታማሚዋ ከመጋቢት 22 አንስቶ ላለፉት ስድስት ቀናት በፅኑ ህክምና ላይ ነበሩ።

ህብረተሰቡ በዚህ ሳይደናገጥ ለተለያዩ ጉዳዮች በአንድ ቦታ መሰባሰብን በማስወገድ፣ እጅን አዘውትሮ በመታጠብ፣ በአካል ንክኪ የሚደረግ ሰላምታን በመተውና አካላዊ መራራቅን (ቢያነስ አንድ ሜትር) ተግባራዊ በማድረግ የበሽታውን ስርጭት እንዲከላከልም ነው ሚኒስትሯ ያሳሰቡት፡፡