በመዲናዋ በግማሽ ዓመቱ በ4 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር የመንገድ ግንባታና ጥገና ተከናወነ
አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በግማሽ ዓመቱ በ4 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር 411 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገናና ግንባታ ሥራ ማከናወኑን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዙ ሥራዎች በወቅቱ አለመፈፀም፣ የመንገድ አካላት ስርቆት እና የመንገድ መብት ጥሰት ፈተና እንደሆኑበትም ተገልጿል፡፡
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢያሱ ሰሎሞን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ 442 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገናና ግንባታ ሥራ ለማከናወን ታቅዶ 411 ኪሎ ሜትር ተከናውኗል፤ በዚህም የዕቅዱን 93 በመቶ መፈጸም መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
352 ኪሎ ሜትር ልዩ ልዩ የመንገድ ጥገና ሥራ ለማከናወን ታቅዶ 360 ኪሎ ሜትር መከናወኑን እና አፈጻጸሙም ከመቶ በመቶ በላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እንዲሁም 89 ኪሎ ሜትር ልዩ ልዩ የመንገድ ግንባታ ሥራዎች ለማከናወን ታቅዶ ከ51 ኪሎ ሜትር በላይ መፈጸሙን ጠቅሰው÷ በዚህም የዕቅዱን ከ57 በመቶ በላይ ማከናወን ተችሏል ብለዋል፡፡
በመንገድ ግንባታ መስክ በታሰበው ልክ አለመፈጸም እና ከወሰን ማስከበርና የግንባታ ግብዓት አቅርቦትጋር የተያያዙ ጉዳዮች ተፅዕኖ ማሳደራቸውን በምክንያትነት አንስተዋል፡፡
5 ሺህ 6 የመንገድ ዳር መብራቶችን ለማዘመን እና ለመጠገን ታቅዶ 7 ሺህ 795 ያህሉን መጠገንና ማዘመን ተችሏል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፡፡
የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችን ጥገናና ጽዳት ማከናወን ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ እንደነበር አስታውሰው÷ በዚህም 266 ኪሎ ሜትር የጥገናና ጽዳት ሥራ መከናወኑን አረጋግጠዋል፡፡
በአጠቃላይ እነዚህን የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎች ለማከናወን 4 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ጥቅም ላይ መዋሉን አቶ ኢያሱ ተናግረዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!