Fana: At a Speed of Life!

የብርቱካን የጤና በረከቶች

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ብርቱካንን መመገብ በርካታ የጤና ጠቀሜታዎች እንዳሉት የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ብርቱካን እንደ ቫይታሚን ሲ፣ ፖታሺየም ፣ካልሺየም ፣ ቫይታሚን ኤ ያሉ ንጥረ ነገሮች እንዲሁም ፍላቮኖይድ እና ካሮቲኖይድ ያሉ በጣም ጠቃሚ ውህዶችን ይዟል፡፡

በቀን አንድ ብርቱካን መመገብ በቀን ውስጥ ማግኘት ካለብን የቫይታሚን ሲ መጠን በላይ እንደሚሸፍን የዘርፉ ባለሙዎች ያካሄዷቸው ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡

ብርቱካንን መመገብ በካንሰር የመጋለጥ እድልን የመቀነስ፣ ቆዳ እንዳይጎዳ የመጠበቅ ፣የደም ግፊትን የማስተካከል፣የልብ ጤንነትን የመጠበቅ፣በደም ውስጥ የሚገኝ የስኳር መጠንን የመቆጣጠር፣የአይን ጤንነትን የመጠበቅ ፣የሆድ ድርቀትን የመከላከል እና የመሳሰሉት የጤና በረከቶች አሉት፡፡

በተጨማሪም በብርቱካን ፍሬ ውስጥ ያለው ቫይታሚን ሲ በሽታ የመከላከል አቅምን በመገንባት በጉንፋን እና በጆሮ ኢንፌክሽን እንዳንጋለጥ ስለሚረዳ ብርቱካን መመገብ ተመራጭ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ቫይታሚን፣ አንቲኦክሲደንትስ እና አልሚ ምግቦች የያዙ ፍራፍሬዎችን አዘውትሮ መጠቀም የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም ከፍ በማድረግ ለሰውነት ጥንካሬ ስለሚረዳ ብርቱካንን አዘውትሮ መመገብ እንደሚመከር ኸልዝ ላይን ጥናቶችን ዋቢ አድርጎ አስነብቧል፡፡

ብርቱካን ፍሬውን ከመመገብ እና በጭማቂ መልክ ከመጠጣት በተጨማሪ በተለያዩ ምግቦችን ውስጥ በግብዓት መልክ ተጨምሮ ልንመገበውም እንችላለን፡፡

አሁን አሁን የብርቱካን ጭማቂ ቀኑን በመልካም ሁኔታ ለመጀመር ከሚረዱ የጤናማ ቁርስ አይነቶች አንዱ እየሆነ መጥቷል፡፡

ብርቱካን በዓለም ላይ በጣም ተወዳጅ ከሆኑት ፍራፍሬዎች ውስጥ የሚመደብ የፍራፍሬ አይነት ሲሆን÷ ሁለት አይነት ዝርያዎች አሉት፤ አይነቶቹም በጣፋጭ እና መራራ ጣዕማቸው የሚታወቁ ናቸው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.