Fana: At a Speed of Life!

አጋር አካላት በኢትዮጵ የዕለት ድጋፍ ለሚፈልጉ 21 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች እርዳታ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አጋር አካላት በኢትዮጵያ የዕለት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 21 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ዜጎች እርዳታ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ፡፡

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ አሁን ላይ በኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው 21 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ዜጎች አሉ፡፡

ከዚህ ውስጥም 4 ነጥብ 6 ሚሊየን የሚሆኑት ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ለእነዚህ ወገኖችም የኢትዮጵያ መንግስት፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሕብረት የእለት ደራሽ ምግብ በዙር እያቀረቡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተለይ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች እስካሁን 149 ሺህ 496 ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ እና ምግበ ነክ ያልሆኑ ግብዓቶች መሰራጨታቸውን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም 1 ሺህ 562 ነጥብ 76 ሜትሪክ ቶን በላይ መድሃኒት እና 4 ሺህ 154 ሜትሪክ ቶን በላይ አልሚ ምግብ ለተጎጂዎች መዳረሱን ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል እስከ ባለፈው ጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ 1 ሚሊየን 113 ሺህ 952 ሊትር ነዳጅ እንዲሁም ለስራ ማስፈጸሚያ የሚውል 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ጥሬ ገንዘብ ለመቀሌ እና ሽረ መላኩን አስታውቀዋል፡፡

አሁን ላይ በትግራይ ክልል ከመንግስት በተጨማሪ 29 አጋር አካላት የሰብዓዊ እርዳታ እያቀረቡ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ በመላው ኢትዮጵያ የዕለት ተረጂዎች ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር የሚቀርበው የዕለት ደራሽ ምግብ በቂ አለመሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡

ስለሆነም የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች እና ሌሎች አጋር አካላት በኢትዮጵያ የዕለት ምግብ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 21 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ዜጎች አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.