Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተጨባጭ ውጤት ተመዝገቧል – አቶ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ወራት በተደረገው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ተናገሩ፡፡
አቶ መላኩ ይህን ያሉት በጎንደር ከተማ የሚኒስቴሩ መስሪያ ቤቱ የ2015 ዓ.ም የስድስት ወራት ተግባራትን እየገመገመ ባለበት ወቅት ነው።
በግምገማው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ያስገኛቸዋል ተብሎ የተለየው የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት የመሳብ ተግባር ባለፉት ወራት ውጤታማ እንደነበር አቶ መላኩ አንስተዋል፡፡
በዚህ ንቅናቄም የወጪ ንግድ መጠንን በ12 ሚሊየን ዶላር ከፍ ማድረግ መቻሉን ነው ያመላከቱት፡፡
የአጎዋ ጫናን በመቋቋም ሚኒስቴሩ ከ194 ሚሊየን ዶላር በላይ 6 አዳዲስ ምርቶችን በመጨመር ወደ ውጭ ገበያ መላክ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
በትግራይ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ኢንዱስትሪዎችን ወደ ስራ ለማስገባት በመቀሌና አካባቢው ያሉት ኢንዱስትሪዎች ጥናት ተጠናቋል ያሉት ሚኒስትሩ÷ ጥናቱም በቅርቡ ይፋ ይሆናል ብለዋል።
የተጀመረው የሰላም ሂደት ለኢንዱስትሪዎች ምርትን በበብዛትና በጥራት እንዲያመርቱ በጎ ዕድል መፍጠሩን አስረድተዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው÷ በክልሉ 28 የኢንዱስትሪ መንደሮችን በማደራጀት በውስጡ 3 ሺህ 200 አልሚ ባለሃብቶች በዘርፉ እየሠሩ ነው ብለዋል።
አማራ ክልል ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነ ነው ያሉት ኃላፊው ÷ ከ344 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ከ2 ሺህ 500 በላይ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።

 

በምናለ አየነው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.