የሀገር ውስጥ ዜና

የተገኘውን የሰላም ጅምር ልንጠብቀው  ይገባል- ጄኔራል አበባው ታደሰ

By Mikias Ayele

January 21, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተገኘው የሰላም ጅምር በሠራዊታችን የጀግንነት ተጋድሎ የመጣ በመሆኑ ልንጠብቀው ይገባል ሲሉ የመከላከያ ሠራዊት ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሠ ተናገሩ፡፡

ጄኔራሉ በምዕራብ ዕዝ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ እንዳሉት÷ ሠራዊቱ  ለሀገሩ ክብር እና ነፃነት ሲል  መስዋዕትነት በመክፈል ሕዝብ እና መንግስት የሰጡትን ተልዕኮ በመፈፀሙ የሚፈለገውን ሰላም ማምጣት ችሏል፡፡

ይህ ሰላም እንደ ሰው ብሎም እንደ ሠራዊት ተፈትነን እና ዋጋ ከፍለን በፈፀምነው አኩሪ ተጋድሎ ያመጣነው  በመሆኑ በእጅጉ ልንጠብቀውና ለዘላቂ ሠላም ተግባራዊነት ቀድመን ልንሰለፍ ይገባል ነው ያሉት፡፡

መላው የመከላከያ ሠራዊታችን ለሀገሩ ሠላም ሲል በርካታ  መሠናክሎችን አልፎ እዚህ መድረሱ ለቀጣይ የሀገራችን ሠላምና ዕድገት ዕውን መሆን ከፍተኛ አሥተዋጽኦ አለው ማለታቸውን የመከላከያ ሠራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡