የቦረና ዞን ከመንግስት በተጨማሪ ሌሎች ተቋማት እና የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረበ
አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ለአምስት ተከታታይ ጊዜ ይጠበቅ የነበረው ዝናብ ባለመዝነቡ በተከሰተው ድርቅ ሰዎች እና እንስሳት ለችግር መጋለጣቸውን ዞኑ አስታወቀ፡፡
በኦሮሚያ ክልል የቦረና ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አብዱሰላም ዋሪዮ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ እስካሁን ባለው መረጃ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ቁጥር ከ604 ሺህ በላይ ደርሷል፡፡
በመንግሥት በኩል ከታኅሣሥ ወር ጀምሮ ለስድስት ወራት የሚዘልቅ ድጋፍ መዘጋጀቱን ጠቁመው÷ ለአብነትም በታኅሣሥ ወር 90 ሺህ 600 ነጥብ 15 ኩንታል ስንዴ፣ 2 ሺህ 718 ሊትር ዘይት፣ 9 ሺህ 60 ኩንታል አተር ክክ ለአንድ ወር የሚሆን ፍጆታ ለህብረተሰቡ ተከፋፍሏል ብለዋል፡፡
12 ቦቴ ውኃ በየቀኑ ለህብረተሰቡ፣ ለጤና እና ትምህርት ተቋማት እየቀረበ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
መንግሥት እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነው÷ ድጋፉ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ የሚደረገው ድጋፍ ይህን ታሳቢ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
በመሆኑም መንግሥት ከሚያቀርበው በተጨማሪ ሌሎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሁለት ወረዳዎች ወባ እና እንደ ጉንፋን ያሉ በሽታዎች መከሰታቸውን ጠቁመው÷ አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
ከድርቁ ጋር በተያያዘ እስካሁን ለህልፈት የተዳረገ ሰው አለመኖሩንም አንስተዋል።
በኦሮሚያ ቡሳ ጉነፋ የሎጅስቲክ ምላሽ መልሶ መቋቋም ዳይሬክተር ደበላ ኢታና በበኩላቸው÷ የጥር ወር ድጋፍ ከትናንት ጀምሮ መጓጓዝ መጀመሩን ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባለፈው ሣምንት 1 ሺህ ኩንታል በቆሎ መላኩን እና በዛሬው ዕለትም 400 ኩንታል በቆሎ እና 400 ኩንታል አልሚ ምግብ እያጓጓዘ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ድጋፉ በዚህ ሣምንት ተጓጉዞ እንዲጠናቀቅ እና ለህብረተሰቡ እንዲሰራጭ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ከታኅሣሥ ወር ጀምሮ እየቀረበ ያለው ድጋፍ በ ‹‹ጆይንት ኢመርጀንሲ ኦፕሬሽን›› በተሰኘ አጋር ድርጅት በኩል ሲሆን ለስድስት ወራት የሚዘልቅ ይሆናል ተብሏል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!