Fana: At a Speed of Life!

ለዓይነ ስውርነት አጋላጭ መንስኤዎች ምንድን ናቸው? ሕክምናቸውስ?

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለዓይነ ስውርነት የሚዳርጉ በርካታ መንስኤዎች መኖራቸውን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በዚህ ጽሑፍ ለዓይነ ስውርነት ከሚያጋልጡ በርካታ መንስኤዎች መካከል ሥድስቱን አንስተን ከባለሙያ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

በጽሑፉ ውስጥ ስለ ዓይነ ስውርነት ሲነሳ በተፈጥሮ ዓይነ ስውር የሆኑትን ሳይሆን የዕይታ ብርሃን ኖሯቸው በሂደት ብርሃናቸውን የሚያጡትን መሆኑን መገንዘብ ይገባል።

በአለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዓይን ሕክምና ክፍል ኃላፊ እና የዓይን ሐኪም ዶክተር ሰሎሞን ቡሳ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ የሞራ ግርዶሽ፣ ግላኮማ፣ ትራኮማ፣ አነጣጥሮ የማየት ችግር (ሪ ፋክቲቭ ኢር)፣ የስኳር ሕመም (ዲያቤቲስ) እና ከመደበኛው የመወለጃ ጊዜ ቀድሞ መወለድ ዓይነ ስውርነትን ከሚያስከትሉ በርካታ መንስኤዎች መካከል ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡

1. የሞራ ግርዶሽ

የሞራ ግርዶሽ በተፈጥሮ ከሚመጡ ለዓይነ ስውርነት አጋላጭ መንስኤዎች አንዱ ሲሆን÷ በኢትዮጵያ ከፍተኛው የዓይነ ስውርነት ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል፡፡

ከ15 ዓመታት በፊት የተካሄደ የጥናት ውጤት እንዳመላከተው÷ በኢትዮጵያ ከሚኖረው ሕዝብ ቁጥር 1 ነጥብ 6 በመቶው የዕይታ ችግር አለበት፡፡ አሁን ሊጨምር እንደሚችል ይገመታል፡፡

በጥናቱ ግኝት መሰረት ካለው የዓይነ ስውርነት ምጣኔ 50 በመቶ የዓይነ ስውርነት ምክንያቱ የሞራ ግርዶሽ መሆኑን ጠቁመው÷ ይህም በተፈጥሮ (አብሮ በመወለድ)፣ በአደጋ (ምት) እና በዕድሜ መግፋት ሊመጣ እንደሚችል የስረዳሉ።

የሞራ ግርዶሽን ቀድሞ መከላከል ባይቻልም ከተከሰተ በኋላ ግን በቀዶ ሕክምና ይስተካከላል ነው ያሚሉት፡፡

2. ግላኮማ

ጤናማ የዓይን ግፊት ከ10 እስከ 21 ድረስ ሲሆን÷ ከ21 ሚሊ ሜትር ኦፍ ሜርኩሪ በላይ ከሆነ ግፊቱ ከፍ ማለቱ ብቻ ሳይሆን በተጓዳኝ የዓይን ነርቭን (ኦፕቲካል ነርቭ) በመጉዳት ዕይታን ይቀንሳል ይላሉ፡፡

ቶሎ ሕክምና ካልተደረገለትም እስከ ዓይነ ስውርነት እንደሚያደርስ ባለሙያው ገልጸዋል።

ግላኮማ በዘር ይተላለፋል፣ ምክንያታቸው በውል ባልታወቁ ሁኔታዎች ይከሰታል፣ አንዳንዴ የዓይን ውስጥ ሕመሞችም ይህን ሊያመጡት ይችላሉ፡፡

ምንም ዓይነት የሕመም ምልክት ስለሌለው ዕይታ ቀስ በቀስ እየቀነሰ ይሄድና ፊት ለፊት ብቻ እንጂ ወደ ጎን ማየት እስከማይቻልበት ደረጃ ያደርሳል ይላሉ ባለሙያው፡፡

ግፊቱ ከፍ በሚልበት ጊዜ ደግሞ የራስ ምታት ያስከትላል፣ በመብራት ዙሪያ እንደ ቀስተደመና የሚመስሉ ቀለማትን ያሳያል፣ ብዥታዎችንም ይፈጥራል፡፡

እንደዚህ በሚሆንበት ጊዜ ተመርምሮ ሕክምና መጀመር ይገባል፤ ሕክምናው ለዕድሜ ልክ የሚሰጥ ሲሆን መቋረጥ የለበትም ይላሉ ዶክተር ሰሎሞን፡፡

የተጎዳውን ነርቭ መመለስ ስለማይቻል ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ግፊቱን ለማውረድ መድኃኒቱ እንደሚሰጥ አስገንዝበው÷ ያለው ዕይታ ባለበት እንዲቆይ (እንዳይጠፋ) ለማስቻል ይህን በማድረግ ዕይታን ማቆየት እንደሚቻል አረጋግጠዋል፡፡

3. ትራኮማ

በኢትዮጵያ ዓይነ ስውርነትን ከሚያስከትሉ መንስኤዎች ትራኮማ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝና በጀርም የሚመጣ ሕመም ነው፡፡

ባብዛኛው የውኃ እጥረት ባለበትና ሞቃታማ አካባቢ፣ ዝንቦች በብዛት በሚፈለፈሉበት፣ ሰዎች ትፍግፍግ ብለው በሚኖሩበትና በሚተኙበት፣ ፎጣና የትራስ ጨርቆችን በጋራ በመጠቀም ይከሰታል፤ ይተላለፋልም።

ይህ ሕመም የዓይንን ቆብ ወደ ውስጥ ቆልምሞ ጸጉሩ የዓይን ብሌንን እየፈገፈገ አቁስሎ ጠባሳ በመፍጠር ብርሃን እንዳይተላለፍ በማድረግ ዓይነ ስውርነትን ያስከትላል፡፡

ስለሆነም የአካባቢ እና የግል ንጽህናን በመጠበቅ ቀድሞ መከላከል እና ሕመሙ ከተከሰተ በኋላም ሕክምና በማድረግ በትራኮማ ምክንያት የሚመጣውን ዓይነ ስውርነት ማስቀረት እንደሚቻል ባለሙያው መክረዋል።

4. አነጣጥሮ የማየት ችግር (ሪ ፋክቲቭ ኢር)

ከአነጣጥሮ የማየት ችግር ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ችግሮች ደረጃቸው የተለያየ ሲሆን በመነጽር የመስተካከል ዕድል እንዳላቸው ይታመናል።

በየትኛውም ሰው ላይ ሕመሙ ቢስተዋልም በይበልጥ ልጆች፣ ወጣቶች፣ ተማሪዎች አነጣጥሮ የማየት ችግሮች በከፍተኛ ደረጃ እንደሚታይባቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።

ቢያንስ ወደ 7 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆነው የዕይታ ችግር ከአነጣጥሮ የማየት ችግር የሚመጣ መሆኑን ዶክተር ሰሎሞን ተናግረዋል።

እነዚህ ሰዎች ተመርምረው መነጽር ሊታዘዝላቸው እና ዕይታቸውን ማስተካከል የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚገባም ይመከራል።

5. የስኳር ሕመም (ዲያቤቲስ)

ሌላኛው የዓይነ ስውርነት መንስኤ በአሁኑ ወቅት ከከተማ እስከ ገጠር እተስፋፋ የሚገኘው የስኳር ሕመም ነው፡፡

በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ሳይስተካከል ሲቀርና ከፍ ብሎ በሚገኝበት ወቅት እንደሚከሰት የሚታመነው የስኳር ሕመም፥ በባህሪው የደም ስሮችን ልፍስፍስ የማድርግ እና በቀላሉ እንዲቀደዱና ደም እንዲረጩ የሚያደርግ ነው ይላሉ ባለሙያው።

በመሆኑም ሕክምና ካልተደረገ በዓይን ውስጥ (ረቲና ላይ) ያሉ ቀጫጭን የደም ስሮች በቀላሉ ደም ሊረጩ ይችላሉ፤ ይህን ተከትሎም ዕይታ ሊጎዳና ሊጠፋ የሚችልበት አጋጣሚ ይከሰታል ነው የሚሉት፡፡

ስለዚህ የስኳር ታማሚዎች ሁልጊዜ የደም ስኳራቸውን እንዲስተካከል ሕክምናቸውን መከታተል ይጠበቅባቸዋል፤ እንዲህ ሲሆን ዕይታቸው ሳይጎዳ ለረጅም ጊዜ ይቆያል ሲሉ ይመክራሉ፡፡

6. ከመደበኛው የመወለጃ ጊዜ ቀድሞ መወለድ

ከመደበኛው የመወለጃ ጊዜ (ዘጠኝ ወር) ቀድሞ መወለድ ለዓይነ ስውርነት ከሚጋልጡ ምክንያቶች አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል።

ሕጻናት በማህጸን ውስጥ እያሉ ሙሉ ዕድገቱን ያልጨረሰው ብሌን (ረቲና) በሚወለዱበት ጊዜ፥ ደም መርጨት፣ የብሌን መላቀቅ ችግር ያስከትልና ለዓይነ ስውርነት ሊያደርስ እንደሚችል ባለሙያው አስገንዝበዋል።

በመሆኑም ያለ ጊዜያቸው የሚወለዱ ሕጻናትን ወደ ሕክምና በመውሰድ ዓይናቸው እንዲመረመርና ተገቢው ክትትል መደረግ ይኖርበታል ነው የሚሉት፡፡

ከ15 ዓመታት በፊት በተካሄደ የጥናት ውጤት እንደተመላከተው÷ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖረው ሕዝብ ቁጥር 1 ነጥብ 6 በመቶው ዓይነ ስውር (የዕይታ ችግር ያለባቸው) ናቸው፡፡ አሁን ሊጨምር እንደሚችል ይገመታል፡፡

ለዓይነ ስውርነት በማጋለጥ ሂደታቸው ቅደም ተከተል መሰረትም÷ የሞራ ግርዶሽ፣ ትራኮማ፣ ግላኮማ፣ አነጣጥሮ የማየት ችግሮች፣ የስኳር ሕመምና የተለያዩ ምክንያቶች፣ የሕጻናት የዓይነ ስውርነት ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡

በአብዛኛው የዓይን ሕመም ሕክምና በሀገር ውስጥ ስለሚሰጥ፥ ህብረተሰቡ በዓይኑ ወይም በዕይታው ላይ ዕክል ሳያጋጥመው ቀድሞ ለመከላከሉ ትኩረት እንዲሰጥና ችግሩ ካጋጠመም ጊዜ ሳያባክኑ ወደ ዐይን ሕክምና ተቋም እንዲሔድ ሲሉ ባለሙያው መክረዋል።

ህብረተሰቡ በልማድ ወደ ሕክምና ተቋም የሚሔደው የዕይታ ችግር ሲደርስበት መሆኑን በመጠቆም፥ አንድ ሰው ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ቢመረመር የዓይኑን በጤንነት የመቆየት ጊዜ ማራዘም ይቻላል ነው ያሉት።

ምክንያቱም በዘር ሊተላለፉ የሚችሉ የዓይን ችግሮች ስላሉና ምንም ዓይነት የሕመም ምልክት ሳያሳዩ (ለምሳሌ ግላኮማ) ዓይነ ስውርነትን የሚያስከትሉ ምክንያቶች ስላሉ ነው ብለዋል።

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.