በማንኛውም ቦታና ሁኔታ ውስጥ ገብቶ ግዳጁን በብቃት መፈፀም የሚችል ጠንካራ ሃይል ተገንብቷል – ሌ/ጄ ዘውዱ በላይ
አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በማንኛውም ቦታ እና ሁኔታ ውስጥ ገብቶ ግዳጁን በብቃት መፈፀም የሚችል ጠንካራ ሃይል ገንብተናል ሲሉ ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ ገለጹ፡፡
ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ ከሰራዊቱ አባላትጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
ሌ/ጄ ዘውዱ በላይ÷ የውስጥም ሆነ የውጭ ፀረ-ሰላም ሃይሎችን በመደምሰስ አንፀባራቂ ድልን ከማስመዝገብ የሚያግደን ሃይል አለመኖሩንም በተግባር እያረጋገጥን እንገኛለን ብለዋል።
ሰራዊቱ እንደባለፉት ጊዜያቶች ሁሉ የተሰጠውን ትልቅ ሀገራዊ ግዳጅ ውጤታማ በሆነ መልኩ እየፈፀመ የሚገኝ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ለተልዕኮው ቅድሚያ ሰጥቶ በመስራት የበለጠ ድል ማስመዝገብ የሚያስችለው የዝግጁነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡
አሁን ላይም ሰራዊቱ በተሰማራንበት ቀጠና በሽብርተኝነት ተግባር ላይ ተሰማርተው የኢትዮጵያ የሰላም ማነቆ እየሆኑ ያሉ ፅንፈኛ ሃይሎችን ዳግም የህዝብ ስጋት እንዳይሆኑ ለማድረግ የማያዳግም ርምጃ እየወሰደ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ከህዝባችን ጋር ያለንን የሰላም እና የልማት ትስስር ይበልጥ አጠናክረን በመቀጠል የኢትዮጵያን ሰላም እና አንድነት አስጠብቀን ማቆየት አለብን ማለታቸውንም ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡