Fana: At a Speed of Life!

ኮኬይን ሲያዘዋውር ተገኝቷል የተባለ የውጭ ዜጋን በማስመለጥ የተጠረጠሩ 2 የፌዴራል ፖሊስ ዋና ኢንስፔክተሮች ዋስትና ታገደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ 27 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም ኮኬን ዕፅ የያዘ የውጭ ዜጋን አስመልጠዋል የተባሉ ሁለት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ኢንስፔክተሮች የተፈቀደላቸው የዋስትና መብት ታገደ።

ተጠርጣሪዎቹ ዋና ኢኒስፔክተር አዲሱ ባሌማ እና ዋና ኢንስፔክተር ጌታነህ ሞገስ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው ታይቷል።

ተጠርጣሪዎቹ ከብራዚል በጁሀንስበርግ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የመጣ ክርስቲያን አንስበር የተባለ የውጭ ሀገር ዜጋ ግለሰብ እንዳይዘዋወርና ጥቅም ላይ እንዳይውል የተከተከለ 27 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም ኮኬይን ዕፅ በሻንጣው ውስጥ መገኘቱን ተከትሎ ግለሰቡ ለሁለቱ ዋና ኢኒስፔክተሮች በታኅሣሥ 4 ቀን 2015 ዓ/ም ተላልፎ መሠጠቱን መርማሪ ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስረድቷል።

ይሁን እንጂ ተጠርጣሪዎቹ ተላልፎ የተሰጣቸውን ግለሰብ በመመሳጠር እንዲያመልጥ አድርገዋል ሲል መርማሪ ፖሊስ የተጠረጠሩበትን መነሻ ለችሎቱ አብራርቷል።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተከናወነባቸው እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን÷ ባከናወነው የምርመራ ሥራ አራት የሰው ምስክር ቃል መቀበሉን ተገልጿል።

መርማሪ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ቤት የብርበራ ሥራ መሠራቱን እና የተደረጉ የሥልክ ልውውጦች ካሉም ለማጣራት ለኢትዮ ቴሌኮም እና ለኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ተቋም ማስረጃ መጠየቁን አብራርቷል።

በተጨማሪም ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከብሔራዊ መረጃ ደኅንነት አገልግሎት ማስረጃ የማሰባሰብ እና የቀሪ ምስክር ቃል የመቀበል ሥራ እንደሚቀረው ጠቁሟል።

ተጠርጣሪዎቹ ከጠበቃቸው ጋር በዚህ ችሎት ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረቡ ሲሆን÷ ከዚህ በፊት ግን ምርመራ ሲደረግባቸው መቆየቱን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስረድተዋል።

ተጠርጣሪዎቹም ፖሊስ ያከናወነው የምርመራ ሥራ በቂ መሆኑን ጠቅሰው÷ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ÷ በዋስ ቢወጡ ማስረጃ ሊጠፋብኝ ይችላል ሲል ሥጋቱን ገልጾ የዋስትና ጥያቄያቸውን ተቃውሞ ተከራክሯል።

መዝገቡን የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ከሰዓት በኋላ በነበረ ቀጠሮ 1ኛ ተጠርጣሪ ዋና ኢንስፔክተር አዲሱ ባሌማ የ40 ሺህ ብር ዋስ አስይዞ ከእስር እንዲፈታ ፈቅዷል፡፡

በተጨማሪም ፍድር ቤቱ 2ኛ ተጠርጣሪ ዋና ኢንስፔክተር ጌታነህ ሞገስ በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈታ መፍቀዱ ተመላክቷል፡፡

ይሁን እንጂ ዛሬ ከሰዓት በኋላ የዋስትና መብታቸው በፍርድ ቤት የተፈቀደላቸው ተጠርጣሪዎቹ የተፈቀደው የዋስትና መብት አግባብ አደለም ሲል የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለት ዋስትናውን አሳግዷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.