አቶ አሻድሊ ሀሰን ለመልሶ-ማቋቋም የሚተገበር ፕሮጀክትን በይፋ አስጀመሩ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 17 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በጸጥታ ችግር የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለማማቋቋም የሚያስችል ፕሮጀክት በርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ይፋ ተደርጓል።
የመጀመሪያ ምዕራፍ የመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክቱ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰንን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ፎቶማንጀሪ ቀበሌ ነው ይፋ የተደረገው።
አቶ አሻድሊ ሃሰን ፕሮጀክቱን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት÷ የክልሉ መንግስት ወደቀያቸው የተመለሱ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እና የተጎዱ መሠረተ-ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም በጥናት ላይ የመሠረተ ሥራ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በቀጣይ በሌሎች አካባቢዎች መሠል ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ትዕግስት ዲቢሳ በበኩላቸው÷ የወደሙ ተቋማትንና ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም 155 ሚሊየን ብር መነሻ በጀት መያዙን ጠቁመዋል።
በመጀመሪያው ዙር የፕሮጀክቱ ትግበራ ማንዱራ፣ ቡለንና ሰዳል ወረዳዎች ተደራሽ የሚደረጉ ሲሆን÷ መሰረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ለማደስና በአዲስ መልክ ለመገንባት እንደሚሠራም ነው የገለጹት።
በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ህብረተሰቡን በስነ-ልቦና የማጠናከር እና በኑሮ በዘላቂነት የማቋቋም ዓላም እንዳለው መጥቀሣቸውን ከመተከል ዞን ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አምስት ዓመት ቆይታ ያለው ፕሮጀክቱ ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚተገበርም ተገልጿል።