Fana: At a Speed of Life!

ለምግብ ዋጋ ንረት ፈጣን እርምጃ ካልተወሰደ ሀገራዊ ስጋት ሆኖ ይቀጥላል- ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 17 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ያለው የምግብ ዋጋ ንረት በአሁኑ ሰዓት በቂ ትኩረት ካልተሰጠውና ፈጣን እርምጃ ካልተወሰደ ሀገራዊ ስጋት ሆኖ እንደሚቀጥል የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የምግብ ዋጋ ንረት መንስኤዎችን እና የወደፊት መፍትሔ አቅጣጫዎችን በተመለከተ ዓውደ ጥናት እያካሄደ ነው።

በዓውደ ጥናቱ ላይ የኢንስቲትዩቱ የግብርና ማዘመን እና የገጠር ልማት ማዕከል ያዘጋጀው ጥናት ቀርቧል።

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ኢንስቲትዩቱ በዚህ በጀት ዓመት ለመንግስት የፖሊሲ አማራጭ የሚሆኑ 50 ጥናቶችን እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

ጥናቱን ለማድረግም ከ50 በላይ ትርፍ አምራች በሆኑና የምግብ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

ያለፉት 10 ዓመታት የዋጋ ሁኔታንም ከስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ዝርዝር በመውሰድ ለጥናቱ ግብዓት መደረጉን ነው የጠቆሙት፡፡

ዋና ዋና የሚባሉ የምግብ አይነቶች በአሁኑ ሰዓት ያላቸው ዋጋ የተካተተ ሲሆን÷ በኢትዮጵያ አሁን ያለው የዋጋ ንረት በቂ ትኩረት ካልተሰጠውና ፈጣን እርምጃ ካልተወሰደ ሀገራዊ ስጋት ሆኖ እንደሚቀጥል ፕሮፌሰር በየነ አስገንዝበዋል።

ጥናቱ ለዋጋ ንረቱ አራት ዋና ዋና ምክንያቶችን ያስቀመጠ ሲሆን÷ እነዚህም የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም፣ የማምረቻ ወጪዎች መናር ፣ የመንግስት ወጪዎችና የገንዘብ ፍሰት ከእውነተኛ ኢኮኖሚ እድገት ጋር የተጣጣመ አለመሆን እና የገበያ ስርዓት አለመዘመን ናቸው ብለዋል።

እነዚህን ችግሮች ከግምት ውስጥ በማስገባም በቀጣይ መንግስት ሊወስዳቸው የሚገቡ የመፍትሔ አቅጣጫዎች በጥናቱ ተጠቁመዋል።

በአጭር ጊዜ ሊወሰድ ይገባል የተባለው መፍትሔም በዋጋ ንረቱ ከፍተኛ ተጎጂ የሆኑትን አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ለመታደግ ከወጪ ገበያ መሰረታዊ የምግብ ፍጆታዎችን በማስገባት አቅርቦትን ማሻሻልና ዘላቂ ድጋፍ ማድረግ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን የገንዘብ ስርጭትና አስተዳደር ከኢኮኖሚው እውነተኛ እድገት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ማድረግ ሌላኛው መፍትሄ መሆኑ በጥናቱ ተገልጿል፡፡

በረጅም ጊዜ የፖሊሲ እርምጃ መሆን ያለበት ደግሞ አነስተኛ አርሶ አደሮችን ምርታማነት በመጨመር መካከለኛ እና ከፍተኛ የእርሻ ኢንቨስትመንቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.