Fana: At a Speed of Life!

በቀላሉ መዳን እየቻለ በመዘናጋት ለአካል ጉዳት የሚዳርገው ሕመም

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም ላይ 3 ሺህ የሚጠጉ የቆዳ ሕመም ዓይነቶች እንዳሉ ይታመናል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት የቆዳ ሕመም በተለያዩ መንስዔዎች ሊከሰት ቢችልም በዋናነት ምክንያቶቹ በሁለት ተከፍለው ሊታዩ ይችላሉ።

አንደኛው እንደ ካንሠር፣ ኩላሊት፣ ስኳር፣ ኤች አይ ቪ/ኤድስ፣ ጉበት፣ እንቅርት እና የመሳሰሉት የውስጥ ደዌ ሕመሞች ጉዳታቸው ሲፀና የጉዳታቸው መጠን በላይኛው የቆዳ ክፍል ላይ ይገለጣል።

ሁለተኛው በውጫዊው የቆዳ ክፍል በቀጥታ የሚደርሱ ችግሮች ናቸው።

በዚህ ረገድ ለምሳሌ፦ ቁስለት፣ አደጋ፣ ከፍተኛ የፀሐይ ብርሃን፣ የውበት ማጉያ (ለፀጉር፣ ከንፈር፣ ፊት፣ እጅ፣ እግር እና ሌሎችም የሰውነት ክፍሎች ማስዋቢያ) የሚሆኑ የሚቀቡ ንጥረ ነገሮች የሚያስከትሉት ችግሮች ይጠቀሳሉ።

በሌላ በኩል ለተለያየ ሕመም ማስታገሻነት የሚወሰዱ መድሃኒቶች እና አመጋገብ በቆዳ ላይ ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡

የቆዳ ሕመም በጀርም፣ በቫይረስ፣ በፈንገስ እና በጥገኛ ተኅዋሲያንም እንደሚከሰት ባለሙያዎች ያብራራሉ።

በአለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቆዳና አባለዘር ስፔሻሊስት ሐኪም የሆኑት ዶክተር ሽመልስ ንጉሤ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ በዓለም ላይ 3 ሺህ የሚጠጉ የቆዳ ሕመም ዓይነቶች እንዳሉ ገልጸዋል።

ከነዚህ መካከል የሥጋ ደዌ አንዱ መሆኑን ጠቁመው፥ ሕመሙ ጾታን እና ዕድሜን እንደማይለይ አመላክተዋል።

በዓለማችን እስከ 200 ሺህ ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ እስከ 3 ሺህ የሥጋ ደዌ ታማሚዎች በየዓመቱ እንደሚመዘገቡ ጠቁመዋል።

የሥጋ ደዌ ሕመም በመተንፈሻ ቧንቧዎች (አፍና አፍንጫ) አማካኝነት ከታማሚው ወደ ጤነኛው ሰው እንደሚሻገር፤ ማስነጠስና ማሳል ደግሞ ዐቢይ መተላለፊያ መንገዶቹ እንደሆኑም ባለሙያው ይናገራሉ።

በአንዳንድ አካባቢዎች ከዘር እና ከአምልኮ (መንፈስ) ጋር አጣብቆ የመገንዘብ ሁኔታ እንዳለ የጠቀሱት ዶክተር ሽመልስ ይህም ፍፁም የተሳሳተ ግንዛቤ መሆኑን ያስረዳሉ።

የቆዳ በሽታ በዘር የማይተላለፍ ሕመም መሆኑንም ነው በአጽንኦት የገለጹት፡፡

በፈረንጆቹ የዘመን ቀመር 1873 ላይ በኖርዌያዊው አርማወር ሃንሰን ÷ የሥጋ ደዌ በባክቴሪያ የሚከሰት ሕመም መሆኑን በምርምር ማረጋገጣቸው በዘር የማይተላለፍ በሽታ ለመሆኑ በማስረጃነት ሊወሰድ እንደሚችልም ጠቅሰዋል፡፡

አንድ ሰው ከ 3 እስከ 5 ዓመታት ድረስ የሥጋ ደዌ ሕመም እንዳለበት ላያውቅ እንደሚችልም ነው ዶክተር ሽመልሽ ንጉሤ የተናገሩት።

ይህም ያለምንም የሕመም ስሜት ምን ያህል ውስጥ ውስጡን እየተስፋፋ እንደሚሄድ ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል።

የሥጋ ደዌ ሕመም ወደ ሰውነት ውስጥ ከገባ በኋላ የሕመም ስሜት የሌላቸው÷ በፊት፣ ጆሮ እና አፍንጫ ላይ የሚታዩ የዕባጭ (ጉብታ) ምልክቶች ከዓይነተኛ ማሳያዎቹ መካከል ናቸው ነው ይላሉ፡፡

በተጨማሪም በማንኛውም የሰውነት ክፍል ነጣ (ገርጣ) ያሉ የቆዳ ቀለሞችን ሊያሳይ እንደሚችልም ዘርዝረዋል። መሠል ምልክቶች ሲታዩ ወደ ሕክምና በመሔድ ምርመራ ማድረግ እንደሚገባም ምክራቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በጊዜው የሕክምና ክትትል ከተደረገ የሚድን እና ከተዘናጉ ደግሞ ሕመሙ እየተሰራጨ እስከ እጅ፣ እግር እና ዓይን አለመታዘዝ ያደርሳል ብለዋል፡፡

በነርቭ ላይ ጉዳት በማድረስ ዕቃ ለማንሳት ወደማይቻልበት ሁኔታ እንደሚያመጣ፤ ዓይንንም እንደፈለጉ መግለጥና መጨፈን እንዳይቻል በማድረግ በአጠቃላይ ሰውነትን ማዘዝ ወደማይቻልበት ደረጃ ያደርሳልም ብለዋል።

የቆዳ ሕመም በሂደት የስሜት ሕዋሳትን እያደነዘዘ በእጅ እና በእግር ቅዝቃዜን እና ሙቀትን እስካለመለየት ይደርሳል።

ሲያይልም በእጅና እግር ላይ ቁስለት ፈጥሮ እስከ አካል መጉደል የሚያደርስ ሕመም መሆኑን አውስተዋል።

አንድ ሰው የሥጋ ደዌ ሕመም ተጠቂ መሆኑ በቤተ ሙከራ ሲረጋገጥ እንደ ሕመሙ ደረጃ ከ6 እስከ 12 ወራት በየዕለቱና በየወሩ የሚወሰዱ መድኃኒቶች ይታዘዙለታል ተብሏል።

መድኃኒቱን መውሰድ በተጀመረ በ3ኛው ሣምንት ሕመሙ ወደ ሌሎች የማይተላለፍበት ደረጃ ላይ ይደርሳል ብለዋል ባለሙያው።

በጊዜው ሕክምና ካልተደረገ የሰውነት ክፍሎች መጣመምን ያመጣል፤ ቁስለቱም የአካል ጉዳትን ይስባል፤ እነዚህን ለማስተካከልም እስከ ቀዶ ሕክምና ያደርሳል ነው ያሉት።

ስለሆነም ሕመሙ የሚያደርሰውን ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎች በመገንዘብ ሁኔታዎች ሳይወሳሰቡ የሥጋ ደዌ ምርመራ በማድረግ የእራስን እና ሌሎችን ጤና መጠበቅ እንደሚገባም መክረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በ2030የሥጋ ደዌን ለማጥፋት ዐቅዶ እየሠራ መሆኑንም አመላክተዋል።

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.