በቀጠናው የተገኘው አንፃራዊ ሰላም ለዕድገት መሠረት የሚጥል ነው – አቶ አሻድሊ ሀሰን
አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመተከል ዞን እና በታላቁ የህዳሴ ግድብ ቀጠና የተገኘው አንፃራዊ የሰላም ለውጥ ለዕድገታችን መሠረት የሚጥል ነው ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ቀጠናውን በጎበኙበት ወቅት ÷ ለሰላም የተዘረጉ እጆች ዛሬም አይታጠፉም ፤ ሠላም የምትፈልጉ ሁሉ ተጠቀሙበት ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ጋር ተቀናጅቶ የተሳካ ስምሪት በመፈፀም ዜጎች በቀጠናው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸውን ያለ ስጋት እንዲከውኑ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል ብለዋል።
በታላቅ መስዋዕትነት የጨበጥነውን ሰላም መልሰን መልቀቅ ትልቅ ዋጋ እንደሚያስከፍል በመገንዘብ የተገኘውን ዘላቂ ሰላም ጠብቆ ማስቀጠል የአካባቢው ህዝብ ከፍተኛ ሃላፊነት መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት።
የክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል አዘነ ሽመልስ በበኩላቸው ÷ የፀጥታ ሃይሉ በመናበብና በመቀናጀት በቀጠናው አስተማማኝ የቅኝት ስምሪት በማድረግ ዘላቂ ሰላም እያረጋገጠ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የፀጥታ ሃይሉ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ሃይሎችን እኩይ ዓላማ ሌት ተቀን እየተከታተለ በማክሸፍ በቀጠናው በሁሉም አካባቢዎች መሠረታዊ የሰላም ለውጥ እያመጣ እንደሚቀጥል ጠቅሰዋል።
ዘላቂ ሰላም የሚገነባው በፀጥታ ሃይል ስምሪት ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ህዝብ የነቃ ተሳትፎ ጭምር መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ሰላም ግንባታና ፀጥታ ሃላፊ አቶ አቢዮት አልቦሮ ናቸው፡፡
በተገኘው የሰላም ድባብ በመታገዝ የህዳሴ ግድቡ ግብዓቶች ሳይቆራረጡ እንዲደርሱ የፀጥታ ሃይሉ ግዳጁን በጀግንነት እየተወጣ እንደሚገኝ መገለጹን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡