Fana: At a Speed of Life!

በድሬዳዋ የነፃ የንግድ ቀጠና በአምራችነት ከተሰማሩ ድርጅቶች ጋር ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 18 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የመጀመሪያ በሆነው በድሬዳዋ የነፃ ንግድ ቀጠና ለመሠማራት ከተዘጋጁ አምራች ድርጅቶች ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመ።

ስምንት አምራች ኩባንያዎችና አራት የፋይናንስ ተቋማት ናቸው በነፃ የንግድ ቀጠናው ገብተው ለመስራት ከስምምነት የደረሱት።

በሥነ ሥርአቱ ላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አቶ አክሊሉ ታደሰ፥ የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና የንግድና የሎጅስቲክስ አገልግሎትን ለማሣለጥ ምቹ በመሆኑ ማክሮ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃትና ባለሃብቶቹን ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አመላክተዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር በበኩላቸው የድሬዳዋ የነፃ የንግድ ቀጠና ከጅቡቲ ወደብ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ የወጪና የገቢ ንግዱ ቀልጣፋ እንዲሆን በማስቻል ረገድ ምቹ ቦታ የተቋቋመ በመሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎች ትርፋማ እንዲሆኑ የሚያስችል እንደሚሆን ገልጸዋል።

የድሬዳዋ የነፃ የንግድ ቀጠና አምራች ተቋማት በተሟላ መልኩ ወደ ስራ በሚገቡበት ወቅት ከሦስት ሺህ ለሚበልጡ ዜጐች የስራ እድል የሚፈጥር እንደሆነ ተገልጿል።

በነፃ የንግድ ቀጠናው በከባድና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተከርካሪዎች መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች፥ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ፋብሪካ ለመገንባት ነው ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር የተፈራረሙት።

አምራች ኩባንያዎቹ በነፃ የንግድ ቀጠናው የማምረት ስራቸውን ለመጀመር ከ6 ቢሊየን ብር በላይ ፈሰስ እንደሚያደርጉ በዚሁ ወቅት ተገልጿል።

የድሬዳዋ የነፃ የንግድ ቀጠና በ150 ሔክታር መሬት ላይ የተቋቋመ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የነፃ የንግድ ቀጠና ነው።

በተሾመ ኃይሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.