Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ከ15 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ 8 ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽሕፈት ቤት ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ሥምንት ፕሮጀክቶችን እየገነባ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ለፕሮጀክቶቹ ግንባታም ከ15 ነጥብ 2 ቢሊየን በላይ በጀት መመደቡ ተገልጿል፡፡

በጽሕፈት ቤቱ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አዲስ አረጋይ ጥላሁን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ፥ በአሁኑ ወቅት የከተማ አስተዳደሩ በትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽሕፈት ቤቱ አማካይነት ሥምንት ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ እያከናወነ ነው፡፡

በግንባታ ላይ የሚገኙት ፕሮጀክቶችም፥ ዓድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ሙዚየም ግንባታ፣ የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ፣ የትራንስፖርት ቢሮ ተቋማት ሕንጻ ግንባታ፣ የካ-2 የመኪና ማቆሚያ፣ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ክላስተር ግንባታ፣ የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላት ግንባታ፣ የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ማስፋፊያ ግንባታ እና የሴቶች የተሃድሶና የመልሶ ማቋቋሚያ ግንባታ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከእነዚህ መካከል የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ክላስተር ግንባታ፣ የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላት ግንባታ፣ የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ማስፋፊያ ግንባታ እና የሴቶች የተሀድሶና የመልሶ ማቋቋሚያ ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክቶች በ2015 ዓ.ም መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም የአዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽንና ኤግዚቪሽን ማዕከል፣ ኤግል ሂልስ (ላጋሬ) ፕሮጀክት እና አዲስ ቱሞሮው ፕሮጀክቶች በአጋርነት (ሽርክና) እየተገነቡ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የግብርና ምርቶች መሸጫ የገበያ ማዕከላት ግንባታም በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 (አያት ሳይት) ፣ ወረዳ 5 (ሰሚት ሳይት) እና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 (ቤቴል ሳይት) እየተከናወነ ነው።

ግንባታቸውም በሥድስት ወራት የሚጠናቀቅ ሲሆን ፥ 6 ነጥብ 1 ቢሊየን ብርም ለግንባታቸው ተመድቧል።

እንዲሁም የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የማስፋፊያ ግንባታ ፕሮጀክት በ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር እየተካሄደ ነው ያሉት አቶ አዲስ፥ ግንባታውን በ18 ወራት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ የሕክምና ጥራትና ደረጃን ማሻሻል እንዲሁም የሆስፒታሉን አቅም በማሳደግ፥ አሁን ላይ መሰጠት የማይችሉ የሕክምና አገልግሎቶችን እንዲሰጥ ለማስቻል ያለመ መሆኑንም ነው የገለፁት።

ከዚህ ባለፈም የአዲስ አበባ ከተማ አነስተኛ እና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ክላስተር ግንባታም ከጥቅምት 2015 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ ግንባታም 4 ነጥብ 7 ቢሊየን ወጪ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለአዳዲስ ኢንዱስትሪያሊስቶች የስራ ዕድል መፍጠር፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በሚመረቱ ምርቶች መተካት፣ የውጭ ምንዛሪ ችግርን መቅረፍ ታሳቢ አድርጎ እየተገነባ ስለመሆኑም ነው የሚያነሱት።

በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ አነስተኛ እና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ክላስተር ግንባታ ፕሮጀክት በተያዘለት 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በጀት ወደ ግንባታ መግባቱን አንስተዋል።

የአዲስ አበባ የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽሕፈት ቤት ከዚህ ቀደም አራት ፕሮጀክቶችን ማለትም፥ የመስቀል ዐደባባይ የመኪና ማቆሚያና እስከ ማዘጋጃ ቤት የመንገድ ማስዋብ ሥራን፣ አብርሆት ቤተ መጻሕፍት፣ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት እድሳትን እና አንድነት የመኪና ማቆሚያን አስገንብቶ ማስረከቡ ይታወቃል።

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.