ፍቅረኛውን ሳኒታይዘር በማርከፍከፍ በእሳት ተቃጥላ እንድትሞት አድርጓል የተባለው ተከሳሽ የሞት ፍርድ ተፈረደበት
አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰብለ ንጉሴ የተባለች የፍቅር አጋሩን ሳኒታይዘር በማርከፍከፍ በእሳት ተቃጥላ እንድትሞት አድርጓል የተባለው ዳግማዊ አራጋው የሞት ፍርድ ተፈረደበት፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ÷ ዳግማዊ አራጋው በፈጸመው ከባድ የግድያ ወንጀል በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ክስ መስርቶ የክርክር ሂደቱን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡
የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያመላክተው ተከሳሽ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 539/1/ሀ ላይ የተደነገገውን ድንጋጌ ተላልፏል ፡፡
ታኅሣሥ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ከሌሊቱ በግምት ከ9፡00 እስከ 10፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ሳሬም ሆቴል ጀርባ ባለው መኖሪያ ቤት የወንጀል ድርጊቱን መፈጸሙ ተመላክቷል፡፡
ተከሳሽ በዕለቱ በፍቅር ግንኙነት አብራው የምትኖረውን ሟች ሰብለ ንጉሴን በተፈጠረ አለመግባባት ድብደባ እና በስለት ጉዳት ማድረሱ በክሱ ተብራርቷል፡፡
በተጨማሪም ሳኒታይዘር ሰውነቷ ላይ በማርከፍከፍ በእሳት እንድትቃጠል ማድረጉን የወንጀል አፈጻጸም ድርጊቱ ያስረዳል፡፡
በደረሰባት አደጋ ምክንያትም የተቃጠለው ሰውነቷ ኢንፌክሽን ፈጥሮ ኢንፌክሽኑ ወደ ሳምባዋና አእምሮዋ ተዛምቶ የደም ዝውውሯና የእስትንፋስ ስርዓቷ ተቋርጦ ሕይወቷ ማለፉ ነው የተገለጸው፡፡
ተከሳሽ ክሱ ተነቦለት የወንጀል ድርጊቱን አልፈጸምኩም በማለት ክዶ የተከራከረ ቢሆንም ተከላከል በተባለበት የወንጀል ድንጋጌ ስር ክሱን ማስተባበል ባለመቻሉ ጥፋተኛ ነህ በማለት የፍርድ ውሳኔ ተላልፏል፡፡
ዛሬ የተሰየመው ችሎትም በከሳሽ ዐቃቤ ሕግ የቀረቡ ማስረጃዎችንና በተከሳሽ የቀረቡ የመከላከያ ማስረጃዎችን መዝኖ ተከሳሹ ጥፋተኛ መሆኑን የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ በበቂ ማስረዳቱ ተገልጿል፡፡
በዚህም ተከሳሽ በሞት እንዲቀጣ ሲል የቅጣት ውሳኔ እንደተላለፈበት ከፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡